Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ኢጣሊያን አድዋ ላይ እንዴት አሸነፈች? ወታደራዊ ስትራቴጂ

የጦርነት ታሪክ ፀሐፍት በአንድ ነገር ይስማማሉ። አንዲት ሀገር በጦር ሜዳ አሸናፊ የምትሆነው በፍትሃዊ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ከሆነች ብቻ ነው። ጦርነቱ ፍትሃዊ ካልሆነ ግን መቼም ቢሆን አሸናፊ አትሆንም። ይህን እሳቤ ይዘን ወደ አድዋ ጦርነት ገፊ ምክንያቶች ስናመራ ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን የገባችበት ጦርነት ፍትሃዊ ሆኖ እናገኘዋለን።

ለምን? የአድዋ ጦርነት መነሻ ዋና ምክንያት የውሃ ዲፕሎማሲ ነው። እንግሊዝ ምስራቅ አፍሪካን በተለይም የዓባይ ወንዝ ተፋሰስን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካላት ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተደረገው የቅኝ ግዛት መስፋፋት እንግሊዝ፣ፈረንሳይ ፣ ቤልጂየም እና ኢጣሊያ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በእርግጥ የኢጣሊያ አመጣጥ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ገና የውህደት ዑደቱን ባለማጠናቀቁ ዘግየት ብላ ነው የተቀላቀለችው።

እንግሊዞች እና ግብፆች በሱዳኖች የደረሰባቸውን ከበባ ለመቋቋም ከኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ጋር ተፈራረሙ፤ የሒዎቴ ወይም የአድዋ ስምምነትን። በሱዳን ከበባ የፈተፀመባቸው የግብፅ እና የእንግሊዝ ወታደሮች በኢትዮጵያ በኩል አድርገው በሰላም መውጣት እንዲችሉ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ። በዚህ ስምምነት እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ወደቦችን ክፍት ለማድረግ ተስማምታለች።ምስራቅ አካባቢ ግብፅ ተቆጣጥራው የነበረውን ወደብም ለቃ ለመውጣት እንዲሁ።

እንግሊዝ ግን ለኢትዮጵያ የገባችውን ቃል አጥፋ በተቃራኒው ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ተገዳዳሪ ሆና የመጣችባትን ፈረንሳይን ለመግታት ኢጣሊያን ጋበዘቻት። ኢጣሊያን በእንግሊዝ ግብዣ የምገባባት የወዲያው ምክንያት ፈረንሳይን መግታት የሚል ቢሆንም የሮም ቄሳር ኃይላት ግን የራሳቸውን ቀመር በአባከሳዊ ስሌት እያሰሉ ነበር። በእንግሊዝ ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት የገባችው ኢጣሊያ ከአፄ ምኒልክ ጋር በውጫሌ ስምምነት ፈረመች።

ያ ስምምነት ግን በመርዝ የተለወሰ ሀረግ እና አንቀጾችን ይዞ ነበር። አንቀፅ 17 የኢጣሊያንኛ ቋንቋ ይዘቱ ፍፁም የተለየ ነበር። ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ የኢጣሊያ የቅኝ ተገዥ ያደረገ ፍሬ ሀሳብ የያዘ ነበር። ኢትዮጵያ ነገሩን ውድቅ አደረገች ። አሁን ሁሉ ነገር ወደ ጦር አውድማ እየዞረ ነው። የቄሳር ኃይላት በዚያ ታላቂቱን ሀገር በቅኝ ግዛት መዳፋቸው ለማስገባት ከቋመጡ ከራርመዋል። ታላቁ አርበኛ ራስ አሉላ አባ ነጋ በዶጋሊ ያደረሰባቸውን ከባድ ኪሳራ እና ውርደት ለመበቀል አሰፍስፈው ተሰልፈዋል።

ታላቂቷ አፍሪካዊት ሀገር የምስራቅ አፍሪቃዋ ኮከብ ደግሞ በታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በኩል አዋጭ ያለችውን ዝግጅት ለአይቀሬው ጦርነት እያዘጋጀች ነው። ሃገራዊ ዝግጅቱ በንጉሠ ነገሥቱ በአፄ ምኒልክ የዘመቻና የጦርነት አዋጅ ይጀምራል።የአዋጁ ይዘት የዘመቻ ጥሪን ለኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሹማምንቶች ኢትዮጵያ በጠላት ጥርስ ውስጥ መግባቷንና የቅኝ ተገዥነት ዕጣፋንታዋ መቃረቡን፣በሕዝቦች የተባበረ ክንድ ግን ጠላትን መመከት እና በቅኝ መገዛት እንደማይቻል የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይህን ታላቅ የጦር ክተት አዋጅ አወጁ።

ከታሪክ መረጃ ምንጮች የምንገነዘበው የምንረዳውም የሩቁንም ሆነ የቅርቡን የዘማች ሠራዊት ኃይል በማደረጃት ከሸዋና ከአካባቢው የተነሳው ዘማች ኃይል ወሎ ወረ ኢሉ ላይ እንዲከት፣ ከጎጃም፣ ከደምቢያ፣ ከቋራ፣ ከበጌምድር እና ከጨጨሆ በላይ ያለውን ሃገር ሁሉ አሸንጌ ላይ እንዲከት፣ የሰሜኑንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ላይ እንዲከት፣ የሐረር ዘማች በአዲስ አበባ በኩል ገና የጥቅምቱ ዘመቻ ሳይጀምር አዲስ አበባ ገብቶ ወረ ኢሉ እንዲከት፣ የወለጋው ሠራዊት መግባት የቻለው ገብቶ በክረምቱ በመስከረም ስለሚበረታ በውሃ ሙላት እንዲቆይ ተደርጓል።

ዋናው ቁም ነገር ግን አዋጁ ሃገራዊ ንቅናቄን መፍጠሩና መተግበሩ ስለነበር በትክክል ተተግብሯል ለማለት ይቻላል። ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ሐይማኖትህን እና ሚስትህን የሚሉ ግዝፈት የሚነሱ ጉዳዮችን ማካተታቸውን ስንመረምር ምን ያህል አርቆ አሳቢ መሆናቸውን እንረዳለን። ሰው በሚስቱ እና በሃይማኖቱ ከመጡበት ቀናኢ ነውና !

የዘመተው ሠራዊት ፍጹም ሕብረብሔራዊ ነበር። እገሌ እና እገሌ ሳይባባሉ ፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ ተቀብለው በሃገራዊ፣ በወገናዊና በባሕላዊ ጉዳዮች የጋራ ትሥሥር፣ የጋራ መግባባትና በኢትዮጵያዊነት ወኔ ተሞልተው ታሪክ ለመሥራት የተሠባሰቡ ዜጎች እንጂ ግዴታ፣ ኃይልና በወቅቱ ሕግ አስገዳጅነት የዘመቱ አልነበሩም።

ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውንና የሃገራቸውን የነፃነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ እንጂ በትናንሽ ቁርሾዎች ልዩነት ፈጥረው ከዋናው ሃገር የመጠበቅ ተልዕኮ ያፈነገጡም አልነበሩም። በዘመቻው ሂደት የታየው የጋራ ክተት ጥሪ፣የታየው የጋራ ዓላማ ፅናት የተሞላበት ረዥሙ የዘመቻ ጉዞ፣ ሣይቸኩሉ ሁሉንም በልባቸው አድርገው የጋራ ድል ማስመዝገቡ የዚያ የአድዋ ዘመቻ የጦር አመራር የጥበብ የምክክር ብስለትና ብቃት ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ የዓድዋን ድል ማስመዝገቡ አስችጋሪ በሆነ ነበር።

 

የዘመቻ ስንቅ ሁኔታ

ከንጉሠ ነገሥቱ ወረገኑ፣ ከእቴጌይቱ ወረገኑ፣በግብር መልክ እንዲገባ በየደረሱበት አካባቢ ከተሰበሰበው የተለያየ የአቅርቦት አይነት ሌላ፣ ዋናው የስንቅ የጀርባ አጥንት ሆኖ ጦርነቱን በብቃት ለማሸነፍ የተቻለው ከዘመቻ ጉዞ ደርሦ መልስን በማካተት በተጨማሪም በውጊያዎችም ወቅቶችም ቢሆን የሕዝቦችን አስተዋፅኦ ይህ ነበር ብሎ መገመቱ ይከብዳል። በተለይ የትግራይ የጦር አውድማዎች አካባቢዎች የነዋሪዎችን ያላሰለሰ ድጋፍ መገመቱ አይከብድም። ወደርየለሽ የአቅርቦት መረባረብ ተደርጓል (ገብረ ሥላሴ ገፅ 227 _268)።

 

በአድዋ ጦርነት የተሰለፈው ዘመቻ ሠራዊ የጦር ኃይሉና መሣሪያ አቅም

ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ተዋፅኦ የነበረ ሲሆን፣ እንደ ዘመኑ አሠራር በተዋረድ የዘመቻ ጥሪ ደርሷቸው የዘመቱ ነበሩ። ባሳለፉበት የውጊያ አውድማዎችና በተሳተፉበት የዓድዋ ግንባር ላይ በታሪክ ውስጥ ሊደመሠሥ የማይቻለውን የዓለም፣ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያን ጥቁር ህዝቦች ድል እውን እንዲሆን አድርገዋል። የተለያዩ የዚያ ሠራዊት አመራርና አባላት በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ውስጥ ወርቅ በእሳት ግሎ እንደሚፈተን በጦርነት የተፈተኑና የጦርነትን ምንነት አብጠርጥረው የሚያውቁ ነበሩ። በኢትዮጵያ ይሁን በኢጣሊያኑ ወገን የተለያዩ ካሊበር አቅም የነበራቸው መድፎች፣መትረየሶችና ሌሎች ነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን በሥራ ላይ ውለዋል።

የኢትዮጵያው ዘማች ሠራዊት የተወሰኑ ከባድ መሣሪያዎች ነበሯቸው። የመሣሪያዎችን ዝርዝርና አቅማቸውን፣ እንዲሁም በሁለቱም ጎን የነበረውን የጦር ኃይሉን አቅም በደንብ ማየት ይቻላል። የኢጣሊያኑ ተዋጊ 56 መድፎችን አሰልፏል። (በርክሌ) ሁለት የኢጣሊያን ባትሪዎች ከባድና ፈጣን ተወንጫፊዎችን እንደተጠቀሙ ዕይታውን ፅፏል። ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ላይ ያሰለፉት 42 መድፎች ነበሯቸው። የወቅቱ ወታደራዊ ጠበብቶች ግን ለዓድዋው ድል ዋነኛ ምክንያት የከባድ መሣሪያው መታጠቅ አልነበረም። የደነደነው ኢትዮጵያዊ የጀግኖች ወኔ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት መድፎች ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ነበሩ። በግዥ፣ በስጦታ፣ አፄ ዮሐንስ ከጉንዳት ና ከጉራዕ ጦርነት ወቅት ከግብፆች የማረኳቸው መትረየሶችና ሌሎች ጠመንጃዎች ሁሉ ተደራጅተው ለውጊያ አገልግሎት ውለዋል። ዋናው ቁም ነገር ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሠራሽ ከባድ መሣሪያዎችን ዓድዋ ጦርነት ላይ መጠቀሟን መገንዘብ ነው!!

የኢትዮጵያዊያኑ የመድፍና የማሽን ጦር መሣሪያዎች በብቃት የመጠቀሙ ሁኔታ በወቅቱ ወታደራዊ ጠበብቶች ተገምግመው፣ የግምገማው ውጤት ሲገለፅ የአድዋ ውጊያዎች የአፍሪቃ ኃይል የሆነው የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት በቅኝ ገዥዎች ሠራሽ መሣሪያዎች ቀኝ ገዥውን ኢጣሊያንን አንበረከከ እንጂ የቅኝ ግዛት ናፋቂዋ ኢጣሊያ በቅኝ ገዥዎች ሠራሽም ይሁን በራሷ በሠራችው መሣሪያ ባለውጤት እንዳልነበረች የዓድዋ ተራሮች ገሃድ አድርገውታል።

በኢትዮጵያ በኩል በፈረንሣይ ገበያዎች በኩል የገቡትን ከባድ መሣሪያዎችን መጠቀም መቻሉን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ተዋጊዎች መሣሪያዎች የኢጣሊያን ኃይል ፀጥ ማሠኘታቸው የኢጣሊያኑ ኃይል ከአላጄና ከመቀሌ የወጊያዎች ሽንፈትና ውድቀት ያለመማራቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። በኢትዮጵያ በኩል ከዘመናዊ ጦር መሣሪያዎች በተጨማሪ ጦርነቱ እየተጋጋለ ሲሄድ ጎራዴና በለበን ነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎችን በመጠቀም ያደረጉት ወሳኝ ውጊያ የአድዋን ጦርነት ድል እንዲያጠናቅቁ ረድቷቸዋል።

 

የአድዋ የጦር አውድማ እና ሦስቱ የውጊያ ቀጠናዎች

ቀዳሚው ፈጠን ብሎ ወደ አድዋው ውጊያ ቀጠና የገባው በጀኔራል አልቤርቶኒ ሥር ቀዳሚውን የኢጣሊያን ባታሊዮን መርቶ የነበረው ማጆር ዴሚኒኮ ትሩኢቶ አስቸጋሪውን የ10 ማይል ጉዞ በመጓዝ እኩለ ሌሊት ላይ ገንደብታ ገባ። የዚህ ኃይል እንቅስቃሴ በየትኛውም ደረጃ ከጀኔራል አልቤርቶኒ ሀሳብ ጋር ስለልተናበበ ሌሊቱን በጨረቃ እየገፋ ሊነጋጋ ሲል በኢትዮጵያ ጦር ካምፕ ውስጥ መሆናቸውን ብቻ ተገነዘቡ።

ኢትዮጵያዊያን በዕሩምታ ተኩስ ጀመሩ። ጠዋት 12 ሠዓት ላይ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲጨምሩ የአድዋው ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ላይ ተጀመረ። ከኢትዮጵያውያኑ 1 ሺህ የሚሆኑት የማጆር ቱሪቶ የመጀመሪያው አስካሪ ባታሊዮን 950 ሰው ብቻ ስለ ነበር ለቁጥር አለመቀራረባቸውም ወዲያኑ በቅፅበት ስለተረዱ፣ ከበባን እንደ አንድ ጥሩ ስልት ወሰዱ። ከወገኑ የራቀው የቱሪቶ ሠራዊት ከጥቅም ውጭ ሆነ። ሠፊ ርቅት በመከሰቱ ጀኔራል አልቤርቶኒ ለማጆር ቱሪቶ መድረስ ከፈለገ ብዙ ሠራዊቱን ለመስዋትነት ይዳርጋል። የኢትዮጵያውያኑ ከበባ ቱሪቶ ወደ ኋላ እንዳያፈገፍግ፣ ጄኔራል አልቤርቶኒም ወደ ፊት እንዳይገሠግሥ አስገደዳቸው።

 

በሁለት ኮረብታዎች (አምባ ምድር) በየሥፍራው የመጠቀም ስልት

የግራው ኮረብታ ጠላትን ከግራ በኩል እንዳያጠቃ የተፈጥሮ መከላከያ ሆኗል።የቀኙ ኮረብታም በቀኝ በኩል ያለው ጠላት እንዳያጠቃ ይከላከላል። ሁለቱን ኮረብታዎች ያገናኘው መሬት ኢትዮጵያውያን መድፎችን ጠምደውበታል። ከዚህ ገዥ መሬት ላይ የአልቤርቶኒ ኃይል ሲንቀሳቀስ በግልፅ ይታያል።

ስለዚህ ሠራዊት ከሠራዊት ጋር በግላጭ መሬት ላይ መዋጋት፣ በከባድ መሣሪያ ሽፋን መስጠት ሆነ። ኢትዮጵያውያኑ የፈለጉትና ያሰቡት ያ ዓይነት አሰላለፍ እንዲሆን ነበር። ሆነላቸው። ከዚህ የቅንጅትና የስልት ሕይወት ውስጥ መድፈኞች፣ባትሪዎች መቀሌ ላይ ከነበራቸው አሰላለፎች ጋር በተመሣሠለ መልኩ አድዋም ላይ ውጤታማነታቸውን አሳዩ።

የሥራ ክፍፍል ተደርጎ መድፈኞችን ማበረታታት፣ እቴጌ ጣይቱ 5 መድፎችን ሥራዬ ብለው በአስተኳሽነት በመሳተፍ ውጊያ ላይ ነበሩ። የራስ መኮንንና የራስ ሚካኤል 15 ሺህ ሠራዊት አልቤርቶኒን በቀኝ በኩል ከበቡት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የንጉሥ ተክለኃይማኖት፣ የዋግሹም ጓንጉልና የእቴጌ ጣይቱ ኃይል አልቤርቶኒን በግራ በኩል ከበቡና የኢጣሊያን ሠራዊት በከበባ አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት ወቀጡት። ይህ የጦር ታክቲክ የኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የውጊያ ስልት ስትራቴጂና ስልትን መጠቀም በትክክል የተተገበረ ነበር። ይህም ኢጣሊያኖች እንዲበታተኑ፣አቅማቸውን እንዲዳከም ያደረገ ስልትና ቅንጅት በመሆኑ የተቀረው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጊዜና እስትንፋስ አግኝቶ ወደ ውጊያው እምብርት ለመንቀሳቀስ ቻለ።

2ኛውጄኔራል ዳቦርሜዳ ለአልቤርቶኒ እርዳታ በመስጠት ወደ ውጊያ በቀኝ በኩል ሲገባ በማሪያም ሻዊት በኩል ወደ አድዋ ፈጥኖ ሲንቀሳቀስ ሌላው ጄኔራል አርሞንዲ ከገንደብታ በፍጥነት ዳቦርሜዳ የለቀቀውን ሥፍራ በመዝጋት ላይ እያለ ዳቦርሜዳ ራሱ አቅጣጫ በመሳት ወደ ግራ ማጥቃት ሲገባው ወደ ቀኝ ተንቀሳቀሰ። የኢትዮጵያውያን ቅንጅት እና ታክቲክ፡ ቶሎ በፍጥነት የኢጣሊያን የአሰላለፍ ምስቅልቅልነትን ተረዱ።

ጊዜ ሳይባክን ስህተቱን ተጠቀሙበት። የዳቦርሜዳ ኃይል ከአልቤርቶኒ ጋር አለመቀናጀቱ ግልፅ ሆነላቸው ማለት ነው። ዳቦርሜዳ ምንም ጥቃት እንደማያደርስ የተረዱት ኢትዮጵያውያን 15 ሺህ እግረኛ ተዋጊዎችን በማስገባት አልቤርቶኒንና ዳቦርሜዳን እንዲነጣጠሉ አደረጉ። ይህ 15 ሺህ ኃይል አደገኛ ኃይል በመሆኑ የዳቦርሜዳን በ3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ለባራቴሪ ባደረገው ሪፖርት ገልጿል። እነዚያ 15 ሺህ ወታደሮች የራስ መኮንን እና የራስ መንገሻ ሠራዊት ነበሩ። ከ3 ሰዐት 30 በኋላ ይህ የሁለትዮሽ ኃይል የኢጣሊያንን የአልቤርቶኒን ተዋጊ ኃይል ወደ ሦስት ስፍራ ተነጣጥለው ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ አደረጋቸው። የእቴጌ ጣይቱ ሠራዊት በራስ መንገሻና በራስ መኮንን ሠራዊት የተቆራረጡትን ኃይሎች ማውደም ጀመረ።

እንደ እውነቱ ከሆነ በሁለቱም ባላንጣዎች ላይ ኃይለኛ ዕልቂትን ያሳየ የተጋጋለው የአድዋ ጦርነት ኢጣሊያኑ ከጧቱ 12 ሰዓት ተኩል ላይ የጀመሩት ማጥቃት ወደ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ተፍረከረኩ። መረጃዎች የሚያስቀምጡት በቅንጅት ማፍረክረክ የተባለው ኢትዮጵያዊው የዚያ ዘመን ታክቲክ ይህ ነበር።

 

3ኛ የውጊያውን ዕምብርት የማፍረስ የመጨረሻው ታክቲክና ቅንጅት

የኢትዮጵያ ሠራዊት የአልቤርቶኒንና የዳቦርሜዳን የክፍተት ስህተት ተገንዝቦ በየስፍራው ጠላትን የመምታት አቅሙን በተግባር ባዋለበት በዚያች ሰዓት በወታደራዊ ጠበብቶች እይታ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለአገራቸው የአድዋን ድል ማስመዝገባቸው የታወቀ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የበርሃው መብረቅ የበጋው ብራቅ የዶጋሊው አራስ ነበር ራስ አሉላ አባ ነጋ በፍጥነት ይህ አጋጣሚ ሳይቆይ እንዲተገበር ወሳኝ የጦር መሪ ሆነዋል። ይህንን ጉዳይ ሲተገብሩ ራስ አሉላ ለንጉሠ ነገሥቱ ያስተላለፉት መልክዕት በመድፍ፣በመትረየስ፣በጠመንጃ ስለወጠርናቸው በአስቸኳይ የኦሮሞ ፈረሰኞች ከራስ ሚካኤል ጦር ውስጥ በብዛትና በፍጥነት አካባቢውን እንዲያጥለቀልቁትና ከምሥራቅ አቅጣጫ መንገድ ዘግተው በጨበጣ የኢጣሊያኑ ኃይል እንዲለቅሙ ብለው ስለተመካከሩ ዉጊያዎቹ ድልን በድል ላይ ጨመሩ።

ጦርነቱ አልቋል ውጊያዎች ግን ቀኑን ሙሉ ተካሄዱ። ከጧቱ 3 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በሌላ አቅጣጫ ወደ ወጊያው የገባው የአርሞንዲ ሠራዊት በተራው ተመታ። በሁሉም አቅጣጫ በጥልቅት የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል በቀለበት ውስጥ በማስግባት ሙት፣ቁስለኛ፣ምርኮኛ ማድረጉን አረጋገጠ። ይህንን የመሰለ የውጊያ አቅም ተጠቅመው በጄኔራል ዳቦር ሜዳ ፣በጄኔራል አርሞንዲ፣በጄኔራል ኤሌና ተዋናይነት በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የሮማ ቄሳር ጦርነት ፣የቅኝ ግዛት ዓላማው አልቤርቶኒና አድዋ የሕልም እንጀራ ሆነ። የአድዋ የድል የሕልም እንጀራ እንዲሆን አደረገው!!

 

ሥለላ እና የአድዋ ድል

በራስ አሉላ አባ ነጋ እና በራስ መንገሻ በኩል በቂ አቅም የነበራቸው እና ግሩም ስራ የሰሩ የመረጃ ሰዎች ነበሩ። በሚስጥር የተዘረጋው የመረጃ መረብ ዕርዳታና ድጋፍ የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት በኢጣሊያ የጠላት ሠራዊት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንዲያሳድር ረድቷል። በሻይ አውዓሎምና በራስ አሉላ እና በራስ መንገሻ ሥር የነበሩት ሌሎች ሰዎች የመሬትና የባህል እውቅት፣የቋንቋ ችሎታና ከኢጣሊያኑም ጋር በነበራቸው የውስጥ ለውስጥ የመረጃ ስራ ብዙ ዘዴ በማካበት የሰጡት መረጃ ኢጣሊያኑን ሠራዊት በሚጎዳና የውጊያውን አጀማመር ኢትዮጵያዉያኑን ዘማች ሠራዊት በሚጠቅም መልኩ በማድረጋቸው አስተዋፅኦቸው እጅግ የጎላ ነበር።የራስ ስብሐትና የደጃዝማች ሐጎስ ከኢጣሊያን ወገን ከድተው ወደ ኢትዮጵያ ሠራዊት መቀላቀል ብዙ መረጃዎችንም ይዞ ስለመጣ ሁኔታዎች ሁሉ ለኢጣሊያ ወራሪ ኃይል እንዳይመቻች አድርጎታል።የዘማቹ ሠራዊት ቆራጥነትና ብርታትም ሌላው ጀብዳዊ የታሪክ አንጓ ነው። ሠራዊቱ አልጋውን ለማቆም እንጂ ለመሸሽ አይፈልግም።አንዱ ወደ ፊት አንዱ ወደ ኋላ አይልም(መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፡የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ) ላይ እንደ ዘገቡት። ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ተስተውሏል፡ኢትዮጵያዊ ፅናት በእጅጉ ተንፀባርቋል ፡በመላው ዓለምም አብርቷል።

 

የአድዋ ድል ለእኛ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካታ የውጭም የውስጥም ድጋቶች ተደቅነውባታል።የምፍትሔ መንገዶችን እያማተረች ፣የቢሆን መላምቶችን እያፍታታች ባለበት ወቅት በእርግጥ የአድዋ ድል እና የዚያ ዘመን የነፃነት አርበኞች ምን መልዕክት ያስተላልፉልናል ብሎ መጠየቅ ብልህነት ይመስለኛል።እስኪ የእነርሱን አስደማሚ ጀብድ ጅማሮ እና ፍፃሜ ሰዓታት ላይ የነበሩ እልሆችን ከታሪክ ድርሳናት እንግለጥ።

ከዘመቻው ጉዞ ሂደት ጀምሮ እስከ ጦርነቱ መጨረሻ ድረስ ዝግመት፣ክፍተት፣ቅፅበትመመካከርና መከባበር በስፋት የነበሩ ክስተቶች ናቸው። በጦርነቱ ወቅት አልጋ በአልጋ የሚሆን ነገር ስለማይኖር በእነዚያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ታልፎ የአድዋ ድል እውን ሆኗል። የእንጢጮን ተራራ በ27 ቀን በፀሐይ በሌሊት በመብራት የተገነባውን፣የተደለደለውን ትቶ እንደ ተመረዘ ጉሬዛ ከሜዳ ላይ ተዘርግፎ እንደ እህል ተወቃ። ስፍራው ቢያበጁ፣መሣሪያ ቢያደራጁ ጉልበትና ብልኃት የእግዚያብሔር መሆኑ በዚህ ተገለጠ (ፀሐፊ ገብረ ሥላሴ ገፅ257) አስፍረውታል።

ከጦርነት ድል በኋላ የተመላሹ ቁጥር ሳስቷል። ዘምተውና በውጊያው ከነበሩት ጀግኖች ውስጥ እነ ፊታውራሪ ገበየሁ ጎራው፣ደጅዝማች ጫጫ፣ደጃች ባሻህ አቦዬ፣ፊታውራሪ ተክሌ፣ቀኝ አዝማች ታፈሰና ሌሎች ያልተተቀሱት ቁጥራቸው የበዛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የአድዋ ጦርነት ወኪል ዋልታና ማገር በነበሩበት ብዙሃን ውስጥ ወደ ቄያቸው አልተመለሱም። የድሉን ጎዳና አፋጥነው በዚያው በእነዚያ የጥቁር ህዝቦች መመኪያ የአድዋ ተራሮች ህያው ሆነዋል። ይህ ትውልድ ከቅድመ አያቶቹ እና አባቶቹ የሰነቁለትን አስተምህሮት በተራው ለወቅታዊው ችግሮች መፍትሄ ሊጠቀምበት ይገባል።

 

ትናንት ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው የውሃ ጦርነት ዛሬም ለሌላ ጦርነት እያዘጋጀን ይሆን ?
ግብፅ እንደ እንግሊዝ ሱዳን እንደ ኢጣሊያ

ጊዜው 19ኛው ክፍለ ዘመን አይደለም።21ኛው ክፍለ ዘመን ነው።ቴክኖሎጂ መር 4ኘው የኢንዱስትሪ አብዮት የተቀጣጠለበት።ምስራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ደግሞ ዛሬም እንደ ትናንቱ ተፈላጊነቱ እጅግ ያሻቀበበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ይህ ቀጣና ከግሪክ እስከ ሮማኖች፡ከኦቶማኖች እስከ ፈርኦኖች፡የቅኝ ግዛት እስከ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ፡ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ገፈታ ቀማሽ ሆኗል። አሁን ደግሞ በአዲሱ የእጅ አዙር ጦርነት መዳፍ ውስጥ ለመግባት በወደብ እና ጦር ሰፈር ግንባታ ከኃያላን እስከ ህዳጣን ከነዳጅ ከበርቴዎች እስከ ኒዩክሌር አረር ባለቤቶች ከፍተኛ ርኩቻ እየተካሄደበት ነው።

ውሃ ውሃ እያልን እንራመድ ! የአድዋ ጦርነት ስረ መሰረት መነሻ እንግሊዝ በኢጣሊያን በኩል የዓባይ ወንዝን የመቆጣጠር ህልም ነበር።የአድዋ ጦርነት ዋና ግብ ጣሊያን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝንበር በተለይም የዓባይ ወንዝን ነበር። ለፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃ ፍለጋ እና በቀጣናው ያላትን ተስፋፋነት እና ተሰሚነት ማጎልበቻ ነበር።ያኔ ጀግኖች አርበኞቻችን የኢትዮጵያ የነፃነት ንስሮች ከሁሉም የሀገራችን ክፍል ነጋሪት ጎስመው ወደ አድዋ ተመሙ። የቄራስ ሃይላት በጥሬ እቃ ምዝበራ የታወሩ ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ያላወቁት ሰላቶዎች በአድዋ ተራሮች የኢትዮጵያን ጀግኖች ጎራዴ ፉጨት መቋቋም ተሳናቸው። የአድዋ ተራሮችም ለእነዚያ ቄሳር ሃይላት ተላላኪዎች የጎን ውጋት ሆኑባቸው። ምዕራባዊያን ለረዥም ዘመን የዘሩት የሀሰት ተረክ በአድዋ ባዶ ሆነ ፡ነጮች በጥቁሮች አይሸነፉም የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለፈፋ በአድዋ ባዶ ሆነ።

አፍሪካዊያን እና መላው የአለም ጥቁር ህዝቦች ብሎም በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩት ሌሎች ሀገራት ፓን ኢትዮጵያኒዝምን እየሰበኩ የቅኝ ግዛት ቀንበርን እስከ ወዲያኛው ጠረማመሱት ። የጣሊያን የጥሬ እቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ የባህል ክለሳ በአድዋ ተደመሰሰ። የዓባይ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ተሸብቦ በአዲሱ የቅኝ ግዛት እሳቤ የተሸበቡት ፈርዖኖች።ዛሬም በ1929 እና 1959 ስምምነት የመሟገቻ እና የአሳሳች ዲፕሎማሲያቸው መጋመጃ አድርገው እየባዘኑ ነው። የግብፆች ግብ እንደ ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት መንፈስ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር ነው።

ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ አይደለም ባህል፣ሃይማኖት ፣ እምነት፣ፍልስፍና፣ ቅኔ እና አፈር ነው። ካይሮዎች ይህን በበላይነት ያለ ማንም ከልካይነት መዝረፍ ይፈልጋሉ አርግጥ ሲሰርፉም ከርመዋል።

ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጀመር ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቋሟ ከኢትዮጵያ ጎን ነበር።ነገረ ኦማር ሀሰን አልበሽር በዳቦ አብዮት ከስልጣናቸው ሲፈነገሉ ውሃው ዲፕሎማሲም አብሮ የተቀለበሰ ይመስላል። ግብፅ እንደ ኢንግሊዝ ሱዳን እንደ ኢጣሊያ እየሆኑ መጥተዋል።

በዚያኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ የዓባይን ወንዝ ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ሱዳን እና ግብፅ የሚገኙ የጥጥር እርሻ ልማቶቿን በማጎልበት ማችስተር እና ላንክሻየር ለ ሚገኙ የአልባሳት እና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎቿ ጥሬ እቃነት በአስተማማኝ ሁኔታ የማቅረብ ህልም ነበራት። ይህን አካሄዷን ለመግታት ሌላኛው የዚያ ዘመን ተፎካካሪ ፈረንሳይ ጂቡቲ ላይ ሆና መስፋፋት ጀመረች።የፓሪስን መንገድ በኢጣሊያ የመዝጋት የእንግሊዝ ሴራ በኢትዮጵያ እውን ሆነ ።

ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ ገባች ። ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ ጦርነት ውስጥ ገቡ በጦርነቱ አዳክሞ ዓባይን መቆጣጠር የእንግሊዝ ከመጋረጃው በስተጀርባ የነበረ እቅድ ነው። ዛሬ ደግሞ ግብፅ ሱዳንን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመላክ ሁለቱን ሀገራት ጦር ለማማዘዝ እያሰፈሰፈች ነው። መገናኛ ብዙሃኖቻቸው 24 ሰዓታት ስለ ሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ በርዕሰ አንቀጽነት እየዘገቡት ነው።

ሱዳንም ኢጣሊያንነቷን አጠናክራ የቀጠለች ይመስላል። ያ ኔ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት ወራ የእኔ ይዞታ ነው በሚል አፍራሽ አካሄድ ስትከተል ነበር። አሁን ደግሞ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት ወራ እኔ ተወጋሁ እያለች የሴራ አቀነባባሪ ወኪሎቿን ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው አይዞሽ የሚሏትን ወገኖች ድምፅ እና ድጋፍ ለማግኘት የአዞ እንባ እያባች ነው።

 

የሱዳን እና ኢጣሊያ ተመሳስሎ

ኢጣሊያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የውሃ ፖለቲካ እና የስትራቴጂክ ቅርምት አፍሪካ ቀንድ ውስጥ የገባችው ገና ሀገረ መንግስቷ የውህደት ጭቃውን ሳያደርቅ ነበር።ሱዳንም አሁን ላይ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ገና የሽግግር የፖለቲካ ትኩሳቷ እና የአልበሽር ዘመን ውልቃቶች ጥሩ ወጌሻ አግኝተው የሱዳናዊያን የምጣኔ ሀብት እድገት ጥያቄ በውል ምላሽ ሳያገኝ ነው። ያኔ እንግሊዝ ኢጣሊያንን ግፊበት እያለች የዲፕሎማሲ ሽፋን ሰጥታታለች።ዛሬም ግብፅ ሱዳንን ግፊበት እያለቻት ነው። የካይሮ ሰዎች ለካርቱም መለዮለባሸሎች በተለይም በአረቡ ዓለም የዲፕሎማሲ ድጋፍ እየሰጧቸው ነው።

የአድዋ ድል ካርድ እዚህ ላይ መሳብ አለበት።እንዴት እና በምን መንገድ የሚለው ጉዳይ ግን ገና ብዙ ተንታኞችን ፡ምሁራን እና ፖሊሲ አውጭዎችን የሚያነጋግር ቢሆንም የእኔ የምላቸውን የሃሳብ ፍንጣቂዎች በተወሰነ ደረጃ ላቅርብ ።ዋናው ጉዳይ ለውሃ ዲፕሎማሲው መፍትሄ ስትራቴጂ መንደፍ ነው። ማርክ ዜቶን እና ዬሮን ዋረን (2006 _Hydro-hegemony – a framework for analysis of trans –boundary water conflicts) በሚለው ጥናታዊ ስራቸው የውሃ የበላይነት ዲፕሎማሲን ማጠናከር የሚቻለው በሦስት ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ በመስራት ነው።አንድም የተፋሰሱን ውሃ ሃብት በብዛት መቆጣጠር፡ሁለትም ከተፋሰሱ አባል ሀገራት ጋር የይስሙላ ትብብር እያደረጉ ታሪካዊ መብትን ማስጠበቅ ሲሰልስ ደግሞ የተፋሰሱ አባል ሀገራት እንዳይጠቀሙ የተለያዩ ዘዴዎችን ገቢር ማድረግ የሚል ነው።

ካይሮ አሁን እነዚህን ሦስት ስትራቴጂዎች ገቢር አድርጋለች ። ውሃውን በብዛት እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡ፍትሃዊ በሚል ግን ኢፍትሃዊ አካሄድ ለማንበር ድርድር እያለች በተቃራኒው በወታደራዊ ሃይል ለማስፈራራት እየሞከረች ነው።አዲሱን የጦርነት ስልት የውክልና እና የእጅ አዙር ጮርነትም በሱዳን በኩል እየሞከረች ነው።

 

የውሃውን እሳት በውሃ የማጥፋት ድህረ አድዋ ወታደራዊ ስትራቴጂ

በዓለም ላይ ከ286 በላይ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ይገኛሉ። በእነዚህ ወንዞች በርካታ ሀገራት የላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አባል ሆነው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ብዙ ጊዜ በላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት ግድብ እና ሌሎች የልማት ስራዎች ሲጀመሩ የታችኞች ተፋሰስ አባል ሀገራት እሮሮ እና እየዬ ዲፕሎማሲያዊ ጩኸታቸውን ያሰማሉ። ሁል ጊዜም መፍትሔ የሚሆነው ግን የተጀመረው ግድብ በድል ሲጠናቀቅ እና ውሃው መፍሰሱን ሲቀጥል ነው። ኢትዮጵያስ ?ኢትዮጵያው ከእነዚያ እንደ አንድ ናት ።

የታላቁ ህዳሴ የህዳሴ ግድብን በፍጥነት ማጠናቀቅ አዲሱን የግብፅ ቅኝ ግዛት መንፈስ ለዘለቄታው መስበር ነው። ጥቅሙም ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም። ለሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጭምር እንጂ። ለምን?የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች እና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አይቻል የሚመልሰለውን የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ ርዕዮት ዓለም ነበር ፓን ኢትዮጵያኒዝም ወደ በኋላ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም የተሸጋገረው።

አሁንም የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ግብፅን እንዴር ተቋቁመን እንችላለን ለሚለው የዘመን ግርጃ መቀልበሻ ጥቁር ማቅ ማውለቂያ ሞዴል ነው። ግድቡ ለአፍሪካዊያን ሌላም የምጣኔ ሀብት ሞዴል ይዞ የሚመጣ ነው!!

እስካሁን በአፍሪካ ግዙፍ ግድቦች በራስ ሀብት ያለ ማንም የውጭ እርዳታ የተገነባ የለም።’ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ይህን የክፍለ ዘመን ግርዶሽ የሚገልጥ ነው። የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአድዋ ድል ብስራት የፓን ኢትዮጵያኒዝም ርዕዮት ዓለም ግማድ ነው!!

 

በሥላባት ማናዬ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.