Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን የመክሰስ አባዜ-ከጥንት እስከ ዛሬ

ማኅሌት ተሾመ

ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ከክስ ያመለጠ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የምዕራቡን ዓለም ለማወቅ ከዛሬ 700 ዓመታት ጀምሮ በሰሜን አፍሪካና በኢየሩሳሌም በኩል ጉዞ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉዟቸው በቬነስ በኩል እያደረጉ እስከ አራጎን(ፖርቹጋል) ድረስ ይዘልቁ ነበር፡ ፡ ይሄንን የኢትዮጵያውያን አሰሳ ተጠቅመው ስለ ሀገሪቱ መረጃ የሰበሰቡ አካላት እነርሱም በበኩላቸው መልእክተኞችንና አሳሾችን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ምዕራቡን ዓለም የፈለጉበትና የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን የፈለገበት ዓላማ ተቃራኒ ነበር፡፡ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን የውጭ ፖሊሲ ‹በእኩልነትና በጋራ ትብብር ላይ የተመሠረተ፣ የጋራ ጠላትን ዒላማ ያደረገ ግንኙነት› ነበር፡፡ የምዕራቡ ዓለም ፖሊሲ ደግሞ ‹ወደ ምሥራቅ ለሚያደርገው አሰሳ ማረፊያ የሚሆነው፣ በቅኝነት የሚያዝ ሀገር ማግኘት› ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዚህ የምዕራቡ ዓለም ግንኙነት አልተመቹም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የሚኮሩ፣ በራሳቸው የሚተዳደሩ፣ የራሳቸው የፖሊሲ ነጻነት ያላቸው መሆናቸው ለዚያ ዘመን ቅኝ ፈላጊዎች የሚዋጥ አልሆነም፡፡ ዛሬም ያለው ችግር ይሄው ነው፡፡

በዚህም የተነሣ በተደጋጋሚ የተሠነዘረውን የፊት ለፊትና ተዘዋዋሪ የቅኝ ግዛት ፍላጎት ኢትዮጵያውያን አምክነውታል፡፡ ምዕራቡ ዓለም ለዚህ የኢትዮጵያውያን መራራ ምላሽ መቅጫ አድርገው ከተጠቀመባቸው ዘመን ጠገብ ስልቶች አንዱ ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መክሰስ ነበር፡፡ በንግሥት ዕሌኒ ወደ ፖርቹጋል ንጉሥ ተልኮ የሄደው አምባሳደር ማቴዎስና በዐፄ ልብነ ድንግል ተልኮ ወደ ፖርቹጋል ሄዶ የነበረው አምባሳደር ጸጋ ዘአብ የገጠማቸውም ይሄው ክስ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያንን እምነት፣ ባህልና ክብር የሚነካ፣ ገጽታቸውን የሚያበላሽ ክስ ነበር የፖርቱጋል ምሁራንና ፖለቲከኞች በአደባባይ ሲያቀርቡ የነበረው፡፡

ከዚያ በኋላም የኢትዮጵያና የምዕራቡ ግንኙነት ምርቅና ፍትፍት ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በባሪያ ንግድ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በሃይማኖት ቀኖና፣ ኢትዮጵያ ስትከሰስ ኖራለች፡፡ ዐፄ ገላውዴዎስ የምዕራባውያንን ክስ ለማስተባበል ሁለት ዐዋጅ አውጥተዋል፡፡ የመጀመሪያው በ1541 ዓ.ም የወጣው የባሪያ ንግድን የተመለከተ ዐዋጅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ‹የሃይማኖት መግለጫ› በሚል ርእስ በ1555 ዓ.ም ያወጡት መግለጫ ነበር፡፡ አውሮፓውያን ኢትዮጵያን በባሪያ ንግድ ሲከስሱ እነርሱ ግን አፍሪካውያንን በባርነት እየፈነገሉ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ አሜሪካ ይወስዱ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን እንስሳትን ሳይገድሉ ይበላሉ፤ የሚኖሩት ዛፍ ላይ ነው፤ ሥራቸው እርስ በርስ መጋደል ብቻ ነው፤ ያልሠለጠኑ ስለሆኑ ልናሠለጥናቸው ይገባል፤ ዓለምም ረስቷቸው፣ ዓለምን ረስተው የሚኖሩ ናቸው፤ ወዘተ. የሚሉ ዕሴት ሰባሪ ክሶች በየዘመኑና በየመዛግብቱ ሲነዙ ኖረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከዐድዋ ድል በኋላ እነዚህ ክሶች እየተባባሱ መጥተዋል። ኢትዮጵውያን ጨካኞች ስለሆኑ በኢትዮጵያ የተማረኩት የጣልያን ወታደሮች በጭካኔ ሊገደሉ ይችላሉ፤ የምርኮኛ መብታቸው አይጠበቅም፤ በቶሎ ካልደረስንላቸው በሕይወት አይተርፉም፤ የሚሉ ክሶች አውሮፓን ሞልተውት ነበር፡፡ ነገሩ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በአውሮፓ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምርኮኞቹ መብታቸው ተጠብቆ፤ ሕክምና አግኝተው፤ አንዳንዶቹም በበቅሎ ተጭነው ነው ለሀገራቸው የበቁት፡፡

የዚህን ዓይነት ክስ ከአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ በኋላም ተከሥቶ ነበር፡፡ ዐርበኞች ጣልያንን ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ እንግሊዞች በአውሮፓ ያሰሙት ክስ ‹የጣልያን ወታደሮች በዐርበኞች እጅ ከወደቁ ሊጨፈጨፉ ይችላሉ› የሚል ነበር፡፡ ይሄንንም ምክንያት አድርገው ቀድመው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ አያሌ የጣልያንን ሀብት ዘረፉ፤ ያልቻሉትንም አወደሙ፡፡ ሀገሪቱንም ለዐሥር ዓመታት በጠባቂነት ለመያዝ ሞከሩ፡፡ እንግሊዞቹ ይባሰ ብለው ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ዕዳ አለባት ብለው በአውሮፓ ክስ አሰምተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያ መንግሥት ለማስረከብ፣ ጣልያንን ለማስወጣት ላደረግነው ትግል 905ሺ ፓውንድ ሊከፈለን ይገባል አሉ፡፡ የእንግሊዝ ሶማሌ ላንድን ለጣልያን ስታስረክብ ግን አምስት ሳንቲም አልጠየቀችም ነበር፡፡

የባሩድ በርሜል የሚለውን መጽሐፍ ያነበበ የማጥላያ ክሱን ደረጃና ዘመናት መመልከት ይቻለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ማኅበር ለመግባት ስታመለክትና ጣልያን በወረራት ጊዜ ለዓለም ማኅበር አቤት ስትል ይሄው ክስ እየተከተላት መከራዋን አይታለች፡፡

ባለፈውም በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከ15 ጊዜ በላይ ለስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ግብጽ ዓባይን ስትገድብ ከቁብ ያልቆጠረው ዓለም፣ ኢትዮጵያ ዓባይን መገደብ ስትጀምር ጉዳዩን የመንግሥታቱ ድርጅት አጀንዳና የምዕራቡ ዓለም የዲፕሎማሲ ክስ መጠንሰሻ አድርጎታል፡፡ በጦርነቱ ወቅት የርዳታ እህል እየተዘረፈ ላልተገባ ተግባር እየዋለ መሆኑን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትናገር ነበር፡፡ ርዳታ ሰጪዎች ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው አልፈውታል። ርዳታው ላልተገባ ነገር ቢውልም፣ ‹የኢትዮጵያ መንግሥት ርዳታ እንዳይገባ እየከለከለ ነው› የሚለው ክስ ነበር ጆሮ ያደነቆረው፡፡ ከ1000 በላይ ርዳታ የጫኑ መኪኖች በጦርነቱ ወቅት ትግራይ ቀርተው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት መንግሥት መኪኖቹ እንዲመለሱ የሚያቀርበውን ጥያቄ ከመቀበል ይልቅ ‹ርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ከልክላችኋል› የሚለውን ክስ ማጮህ ነበር የተፈለገው፡፡

እነዚህ አዝማሚያዎች አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን በርዳታ እህል ዝርፊያ ወደ መክሰስ፡፡ የርዳታ እህል በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ላልተገባ ተግባር የዋለበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለውም የተስተካከለ የርዳታ ሥርጭት አሠራር በመዝርጋትና ችግር ሲያጋጥም ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርመራ በማድረግ ነው፡፡ ርዳታ ከሰብአዊነት በላይ ፖለቲካዊ ባሕሪው ያመዝናል፡፡

በተለይም ሀገሮች የሚሰጡት ርዳታ የፖለቲካ ግብ ማስፈጸሚያ ነው፡፡ ለዚህ ነው ርዳታ አልቀበለም ማለት ከእነዚህ ሀገሮች ጋር ወደ ግጭት የሚያስገባው፡፡ ርዳታ መስጠት ፖለቲካዊ እንደሆነው ሁሉ፤ ርዳታ ማቆምም በፖለቲካዊ ውሳኔ የሚከናወን ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ተግባር ነው፡፡ ርዳታን በተመለከተ የሚሰጡ መግለጫዎችም ይሄንኑ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያስፈጽሙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ከርዳታ ድርጅቶች ቀጥለው የምግብ ርዳታ እንዲሰጥ የሚወተውቱት የለጋሽ ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሆናቸው የርዳታውን ፖለቲካዊ ሚዛን የሚሳይ ነው። ርዳታ ምን ያህል የፖለቲካ ውሳኔ ማስፈጸሚያ እንደሆነ ለማየት ኢትዮጵያና ሶማልያ ውስጥ የተከሠቱ አራት የታሪክ አጋጣሚዎችን እንመልከት። በ1970፣ በ1977፣ በ1944- 70 እና በ2012-13 ዓ.ም።

በ1969/70 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ ርሃብ ተከስቶ ነበር። በጊዜው የነበረው የደርግ መንግሥት በሰኔ 1970 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በወሎና በትግራይ 1ነጥብ5 ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸውንና 400 ሺህ ኩንታል ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ተናገረ። በአውሮፓና በአሜሪካ የነበሩ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች መጀመሪያ ያሰሙት ክስ ‹ውሸት ነው› የሚል ነበር። የደርግ መንግሥት የተመረተውን ምግብ ለወታደሮቹ ስላዋለው፤ የቀረውንም ለመሣሪያ መግዣ ወደ ሶቪየት ስለጫነው ነው› ተባለ። አሜሪካኖች ይሄንን የሚሉት ኢትዮጵያ የከፈለችበትን

መሣሪያ አንሰጥም ብለው ካስቀሩባት በኋላ ነው። በ1971 ዓ.ም ጥቅምት ወር ኮሎኔል መንግሥቱ ራሳቸው በሚዲያ ወጥተው ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገለጡ። አብዛኛው የምዕራቡ ፖለቲከኛና ሚዲያ ነገሩን ለፖለቲካ ልዩነት ማራገቢያና ከሶቪየት ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማጠልሺያ ነበር የተጠቀመበት። ‹ኢትዮጵያ ምግብ ከገበሬው ነጥቃ ለወታደሩና ለመሣሪያ መግዣ አዋለችው› የሚል ነበር የሚሰማው ክስ።

በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተለመደው ረሃብ ተከሠተ። የርሃብተኛው ብዛት እስከ አምስት ሚልዮን እንደሚደርስ፣ ከእነዚህ መካከል 700 ሺዎቹ አስቸኳይ የምግ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አዲስ አበባ ለሚገኙት ኤምባሲዎች አሳወቀ። ምላሹ ግን ከተጠበቀው እጅግ ያነሰ ነበር። ፖለቲካ ዋናው ምክንያቱ ነበር። ለርሃብተኞች ከመድረስ ይልቅ የደርግን መንግሥት መክሰስና መጉዳት ዋና ዓላማ ሆነ። በዚህ ዘመን ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሶሻሊስት ያደሉበት ዘመን ስለነበር የአሜሪካ ርዳታ እጅግ ቀንሶ ነበር።

ሐዋርድ ዎልፕ፣ ሚኪ ሊላንድ፣ ዊሊያም ኤች፣ ግሬይ የተባሉት የኮንግረስ ሰዎች እየወተወቱ፣ ጆን ዳንፎርዝን የመሰሉ ሴናተሮች እየጮኹ የሬገን አስተዳደር ግን ‹ምግብን ለፖለቲካ ዓላማ› በመጠቀም ጆሮ ዳባ ልበስ አለ። ለሚጠየቀው ጥያቄ ዋና መከራከሪያው ‹የርዳታው እህል ወደ ተረጂዎች ሳይሆን ወደ ወታደሮች ይሄዳል› የሚል ነበር። የዩኤስ ኤይድ ሁለት ሠራተኞችም ‹የርዳታ እህል እየተሸጠ ከሶቪየት ለመሣሪያ መግዣ ይውላል› የሚል ክስ አሰሙ። ከዚህ ብሶ ‹መንግሥት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የምግብ እጥረት የለም› ማለትም ጀመሩ። የዚህ አዝማሚያው ሌላ ነበር። ርዳታ በሌላ በኩል ይግባ ለማለት።
(እኤአ 1982) በአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባለሙያዎች የተካሄደው ምርመራ ግን የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ክስ የተጋነነ መሆኑን አሳይቷል። በሚያዝያ 1975 ዓ.ም በርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በኩል ታይተዋል የተባሉ የሙስናና የአስተዳደር ችግሮች ኃላፊዎችን በመቀየርና አሠራሮችን በማሻሻል ተስተካክለው ነበር።

እኤአ በ1984 (1976 ዓ.ም) የዩኒሴፍ ባለሙያዎች 2000 ማይልስ ያህል በኢትዮጵያ ተዘዋውረው የተመለከቷቸውን የርዳታ ማከማቻና ማከፋፈያ ሥፍራዎች መሠረት አድርገው በሠሩት ሪፖርት፣ የሁለቱ መንግሥታት ክስ ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል።

የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ለሁለት ዓመታት ርዳታን ከኢትዮጵያ በማስቀረት የሠሩት ሥራ ዓላማ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን መንግሥት አስጨንቆ ለመለወጥ (regime change) የታሰበ መሆኑን በጥቅምት 1977 ዓ.ም ሬቨረንድ ቻርለስ ኤልዮት የተባሉ የክርስቲያን ርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር ገልጠው ነበር። ‹የተባባበሰ ችግር ከተከሠተ፣ ሥርዓቱን እንደገና ሊቀይረው ይችላል ብለው አስበዋል› ሲሉ ለሳምንታዊ የእንግሊዝ ጋዜጣ ለኦብዘርቨር ተናግረው ነበር። የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ለመለወጥ የወሎ ርሃብ እንዳገለገለው ሁሉ የ77ቱን ረሃብም የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን መንግሥት ለመጣል እንጠቀምበት ዓይነት ነው።

በመንግሥት በተያዙ አካባቢዎች እጥረት የለም ብለው ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ያመኑት ምዕራባውያን፣ በዚህ ጊዜ በሱዳን በኩል ወደ ትግራይ ርዳታ እንዲገባ የደርግ መንግሥትን ቁም ስቅሉን አሳዩት። ደርግ በደረሰበት ጫና ምክንያት በሱዳን በኩል ርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ ፈቀደ። ይህ ርዳታ ግን ብዙ መዘዝ ይዞ መጥቶ ነበር። አንዱን ብቻ በዚህ ጊዜ ማየት ተገቢ ነው። ይሄንንም በወቅቱ የነበሩት የሕወሓት ሰዎች አረጋዊ በርሄ(ዶር) እና ገብረ መድህን አርአያ በየመጽሐፎቻቸው አስፍረውታል። የርዳታ እህል ለተረጂዎች ሳይደርስ ይሸጥ ነበር። ለወታደራዊ አገልግሎት ይውል ነበር። ይሄ ሲሆን ግን የርዳታ ሰጪ ሀገሮችና ተቋማት ያውቁ ነበር። ሆኖም ዓላማቸው ደርግን መውጋት በመሆኑ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች በዝምታ መመልከታቸውን ገልጠውታል። ለዚህም ነው ርዳታ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ነው የሚባለው። ደርግን ባደረገውም ባላደረገውም ይወቅሱ የነበሩ ምዕራባውያን፣ ዐማጽያኑን ግን ‹መሐረቡን አላየንም› ብለው አልፈዋቸዋል።

በ1964 ዓ.ም አካባቢ የአሜሪካና የሶማሊያ የጦር ግንኙነት ሲጀምር የአሜሪካ ርዳታ በዚያ ጊዜ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ርዳታ ኤጀንሲ(AID) በሚባለው ተቋም በኩል ሶማልያ መድረስ ጀመረ። ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ግጭት ስለነበራት የአሜሪካን ርዳታ ለወታደራዊ ተግባር ታውለው ነበር። የአሜሪካ ባለ ሥልጣናት ይሄን ያውቃሉ። ለጋራ ጥቅማቸው ሲሉ ግን ባላየ አልፈውታል። እኤአ በመጋቢት 1986 በጄኔራል አካውንቲንግ ቢሮ አማካኝነት ይሄ ጥፋት ተጠንቶ “Famine in Africa: Improving Emergency Food Relief Programs” በሚል ርእስ ለአሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ ነበር። የአሜሪካ ፖለቲከኞችና ሚዲያ ግን በቸልታ አልፎት ነበር። የዚህም ምክንያቱ ኢትዮጵያንና ሌሎች ሶሻሊስት የአፍሪካ ሀገሮችን ‹ርዳታን ላልተገባ ዓላማ አውላችኋል› በሚል ክስ ተጠምደው ስለነበረ ነው። በተለይም በ1977 ዓ.ም አካባቢ በነበረው ከባድ ድርቅ ጊዜ የርዳታ ምዝበራው ተባብሶ ነበር። ከ16 ሺህ ቶን ርዳታ መካከል 12 በመቶው ብቻ ለተራቡት ይደርስ ነበር። 9 በመቶው ለሶማሊያ ወታደሮች ሲላክ፣ 21 በመቶ ደግሞ ለሌሎች መንግሥታዊ አካላት ይደርስ ነበር። 58 በመቶ ደግሞ ፈጽሞ አይሠራጭም። ይሄን ሁሉ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ‹የወዳጅ ገመና አይነገርም› ብለው አልፈውታል።

በቅርቡ በ2012 እስከ 2013 ዓ.ም በሰሜኑ ጦርነት የተከሠተውን ደግሞ የዓይን እማኙ ኦማሞ (S.E.Omamo)፣ “At The Center of the World in Ethiopia” በተሰኘው መጽሐፉ በዝርዝር ገልጦታል። ኦማሞ፣ በጦርነቱ ጊዜ ታላላቅ “ዓለም አቀፍ ተቋማት” ሲጫወቱ የነበረውን አፍራሽ ኢትዮጵያን የመክሰስ ሚና ከገጠመኙ ተነሥቶ ይተርካል። ኦማሞ እአአ ከ2018 – 2021 መጨረሻ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ነበረ። “የትግራይ ረሃብ” የሚባለው ትርክት “በችግር ነጋዴዎች” የተፈጠረ ክስ እንደነበር ይተርክልናል።

የችግር ነጋዴዎች ከመቀሌ እስከ ሮም፣ ከጀኔቫ እስከ ኒውዮርክ በፈጠሩት ሠንሰለት እንዴት ይሄን የሐሰት ክስ እንዳራገቡት ስትሰሙ ኢትዮጵያን መክሰስ ኢትዮጵያን የመታገያ አንዱ የፖለቲካ መንገድ መሆኑን ትረዳላችሁ። “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ” በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ የፈጸመው ግፍ ዓላማ ኢትዮጵያን ለመክሰስ ምቹ ስላልሆነለት ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጸመውን ግፍ በዝምታ እያለፈ በሌላ በኩል ተፈጽሟል ስለሚለው የሐሰት ክስ ሚዲያዎቹን ሁሉ ያስጮህ ነበር። ትግራይን በተመለከተ ሲወጡ የነበሩ የሞት፣ የረሃብና የችግር ሪፖርቶች እንዴት ሲቀመሩ እንደነበሩ ከመጽሐፉ ታነባላችሁ።

ስለተዘረፈ ነዳጅና እህል፣ ቀልጠው ስለ ቀሩ የርዳታ መኪኖች አንዳች እንዳይነሣ ሲደረግ ነበር። “በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ” ስም ስለ ኢትዮጵያ ሲሰጡ የነበሩ መግለጫዎች፣ ትዊቶችና ማሳሰቢያዎች ችግሩን በማያውቁና ፍላጎታቸው ኢትዮጵያን መክሰስ ብቻ በሆኑ ኃላፊዎችና የጀርባ ገፊዎቻቸው የሚመሩ መሆኑን ታረጋግጣላችሁ። በኢትዮጵያ ላይ “ታላላቅ ሀገሮች” የሚከተሉት አካሄድ ከዘረኝነት ጋር ያለውን ትሥሥር ስትረዱ ታዝናላችሁ።

እነዚህ ከላይ የተገለጡ አራት ማሳያዎች የርዳታ እህልን በተመለከተ የሚሰጡ መግለጫዎች ከመቆርቆርና ለድኾች ከማዘን የሚመነጩ ሳይሆኑ፤ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማስፈጸም ከሚመነጭ ፍላጎት የሚነሡ መሆናቸውን ያሳዩናል። ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሰሞኑ የተነሡ ክሶች በዋነት የሚመነጩት ከተፈጠሩ ስህተቶች ሳይሆን ከፖለቲካዊ ፍላጎት ነው። ነገሮቹን ነጥብ በነጥብ እንመልከታቸው።

  1. የርዳታ እህል አይሰረቅም ወይ? ከተባለ፣ የርዳታ እህል ላልተገባ ተግባር ሊውል የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። የኢትዮጵያ የርዳታ እህል ሥርጭት ከዚህ ነገር ሙሉ በሙሉ የነጻ የበቃ ነው ለማለት አያስደፍርም። አሁን ያለው ጩኸት ግን ከፍየሏ በላይ ነው። 70 በመቶው የርዳታ እህል የሚሠራጨው በራሳቸው በርዳታ ሰጪ ተቋማት በኩል ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለተፈጠረው የሥርጭት ክፍተት 70 በመቶን ተጠያቂነት ይወስዳሉ ማለት ነው። ወይም ደግሞ ቢያንስ የርዳታ ሰጪ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እጅ አለበት። ይህ ግን በፍጹም እንዲነሣ አልተፈለገም።
  2. ከዚህም በተጨማሪ የርዳታ እህል ሥርጭት ላልተገባ ተግባር መዋሉን የሚያመለክት ፍንጭ ሲገኝ ርዳታው ከሚሰጥበት ሀገር የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ሁሉንም የተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ ይደረጋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሄን ምርመራ ከረጂ ተቋማት ጋር በጋራ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። ታድያ አስቀድሞ ክሱን ማጯጯህ ለምን አስፈለገ? ከዚህ በፊት በነበሩት የርዳታ ስርቆት ተግባራት ጊዜ ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ አካላትስ አሁን ለምን ተጣደፉ?
  3. በማሳያነት የሚቀርቡ ሁነቶችስ፣ ከተባለም፣ የርዳታ እህል ተሸጧል ለማለት የሚቀርቡት ሁለት ሁነቶች አጠራጣሪ ናቸው። የመጀመሪያው በገበያ ላይ መገኘቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በወፍጮ ቤት መታየቱ ናቸው። ርዳታ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ምክንያቶች ይሰጣል። የመጀመሪያው በምግብ ለሥራ ፕሮግራም ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በቀጥታ ለተረጂዎች የሚሰጥ ነው። በሁለቱም መልኩ ርዳታው ለገበያ የሚቀርብበት ዕድል አለ። ተረጂዎች የርዳታ እህሉን ብቻ አይፈልጉትም። የርዳታ እህሉን በመሸጥ የሚገዟቸው ነገሮችም አሉ። እነዚህን ነገሮች ለመግዛት ሲሉ የርዳታ እህሉን ወደ ገበያ ያወጡታል። የወፍጮ ቤቱም ጉዳይ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነው።
  4. የርዳታ ስንዴው ስርቆት ለምን ከኢትዮጵያ የስንዴ አምራችነት ጋር እንዲያያዝ ተፈለገ? የሚል ነጥብ ሊነሳ ከቻለም፣ የኢትዮጵያ የስንዴ ሉዓላዊነት ሀገሪቱን አንድ ርምጃ ወደ ላይ የሚወስዳት ነው። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስንዴ ግዥ ከ710 ሚልዮን ዶላር በላይ ታወጣለች። የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎ ከ65 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ በሀገር ውስጥ ሲመረት 30 በመቶው ከውጭ ይገባ ነበር። ይሄን ለማስቀረትና ራስዋን ለመቻል በበጋና በመኸር የስንዴ ልማት ላይ ተሠማርታለች። በዚህም የተነሣ ከውጭ ስንዴ በግዥ የማታስገባበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። ይሄ ያላስደሰታቸው አካላት ገና ከመነሻው ዕንቅፋት ሲፈጥሩ ነበር። ኢትዮጵያ ምርቷን ስታበስር ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ ስንዴ ከዩክሬይን መነሣቱን ሚዲያዎች አራገቡ። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ስንዴ ለመሸጥ ስትነሣ በወረደ ዋጋ እነርሱ ማቅረብ ጀመሩ። አንዳንድ ሀገራትን የኢትዮጵያን ስንዴ እንዳይገዙ ጫና አደረጉባቸው። ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሸጠችው ስንዴ የርዳታ እህሉን ነው ተብሎ እንዲታሰብ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ተጀመረ። የዚህ ሁሉ ዓላማ በተለመደው የኖረ ዘፈን ሀገሪቱን መክሰስ ነው።
  5. ችግሩን መፍታት ወይስ ድኾችን መቅጣት፣ የሚል ከፍ ያለ የሞራል ጥያቄ ይነሳል። ምክንያቱም ሊሆን የሚገባው ችግሩ ተከስቷል ቢባል እንኳን መፍትሔው በጋራ የምርመራ ቡድን ችግሩን አጥንቶ መፍትሔ መስጠት ነው ወይስ ርዳታው የሚሰጣቸው ድኾች መቅጣት ነው፡፡ የሚል የሞራልም የአካሄድም ጉዳይ ይነሳልና ነው። ከዚህ በፊት በጦርነቱ ጊዜ ርዳታ ተገቢ ላልሆነ ተግባር እየዋለ መሆኑ ሲነገር የምዕራብ ሀገሮችና የርዳታ ድርጅቶች ምላሽ ‹በጥቂት ጥፋተኞች ምክንያት ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ድኾች መቅጣት የለብንም› የሚል ነበር። በዚህም የተነሣ ስለ ችግሩ መስማትም ሆነ መወያየት አልፈለጉም ነበር። ከዚያ ይልቅ ‹ያልተገደበ የርዳታ ማቅረቢያ መንገድ (unhindered humanitarian access)› ይሰጠን የሚል ነበር ጫናው። ታድያ ዛሬ ምን ተከሠተ፡ ፡ ሀገሮቹ አልተቀየሩም፤ ድርጅቶቹም እነዚያው ናቸው። ምርመራውንና ርዳታው ጎን ለጎን ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው የሚሰኘውም ይሄው ነው።

በ1970ዎቹ አጋማሽ የአሜሪካ የእርሻ ሚኒስትር የነበረው ኧርል ቡትዝ ‹ምግብ የጦር መሣሪያ ነው፤ በመደራደሪያ ቦርሳችን ውስጥ ከሚገኙት መሠረታዊ መሣሪያዎች አንዱ ነው› ብሎ ነበር። የኤሊኖይስ ገበሬ የነበረውና በሮናልድ ሬገን የእርሻ ሚኒስትር ሆኖ የተመደበው ጆን ብሎክ እኤአ በ1980 ‹በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን ከሚያስችሉን የጦር መሣሪያዎች ዋናው ምግብ ነው ብዬ አምናለሁ› ብሎ አጽንቶታል። የምግብ ርዳታ ከሰብአዊ ርዳታነቱ ይልቅ የጦር መሣሪያነቱ የበለጠ ነው። በርግጥ ርዳታን እምቢ ለማለት በሚያስችል ዐቅም ላይ ላንሆን እንችላለን። ርዳታውም የሚያስፈልጋቸው ሚሊዮኖች ወገኖች አሉን።

ከግማሽ ምዕተ ዓመት የተሻገረ የምግብ ርዳታ ታሪክም አሳልፈናል። ሆኖም ርዳታ ተረጂዎችን ከማብዛት አልፎ ያመጣልን መሠረታዊ ለውጥ የለም። የፈጠርነው የተረጂነት ባህል ግን ሉዓላዊነታችን የሚገዳደር ሆኗል። የአሜሪካ የርዳታ ድርጅት(USAID) እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራውን የጀመረው እኤአ በ1961 ነው።

በነጻነታችን እንደልብ እንዳንኮራ የሚያደርገን ተረጂነታችን ነው። ርዳታ እንዳይቀርብልን ከምናደርገው ርብርብ ይልቅ ርዳታን ለመተካት የምናደርገው ትግል ሙሉ ነጻነት ያመጣልናል። የሰሞኑ ‹እህል አንሰጣችሁም› ማስፈራሪያ ከሚያመጣብን ኀዘን ይልቅ የሚያስከትልብን ንዴት ከበለጠ እንለወጣለን። ጎንበስ ብለን ረጂዎችን ከመለመን ይልቅ ጎንበስ ብለን ምድራችንን ብንለምናት ኩራትና እራት አንድ ላይ ትሰጠናለች። ያለበለዚያ ግን እነርሱም መክሰሳቸውን አይተዉ፣ እኛም መሟገታችንን አናቆምም።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.