Fana: At a Speed of Life!

ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሂደትን ተመለከቱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በእቴጌ መነን የልጃገረዶች ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሂደትን ተመልክተዋል ።

የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ41 የመፈተኛ ጣቢያዎች በመሰጠት ላይ ይገኛል ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በትምህርት ቤት ተገኝተው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ  ተማሪዎችን አበረታተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በጉብኝቱ ወቅት ዛሬ አለም አቀፉ የሴቶች ቀን በሚከበርበት እለት ሴት ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ተገኝተው የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ማበረታታቸው የተለየ ደስታ እንዳሳደረባቸው ጠቁመዋል ።

በዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በሴትነታቸው ሳይሆን በውጤታቸው ተለይተው የመጡ እንደመሆኑ ተፈታኞቹ ፈተናቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈተኑ ለማበረታታት መገኘታቸውን መግለፃቸውን ከከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በርካታ ሴቶች እውቀት እያላቸው እድሉን ባለማግኘታቸው ብቻ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ሳይሆኑ መቅረታቸውን  የገልፁት  ወይዘሮ አዳነች በእቴጌ መነን ልዩ የልጃገረዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ በዛሬው እለት በመላ ሀገሪቱ ፈተናውን በመውሰድ ላይ ለሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎችም መልካም እድል ተመኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣  የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ኃላፊ ዶክተር ዴላሞ ኦቶሬ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቾ በተለያዩ የመፈተኛ ጣቢያዎች ላይ በመዘዋወር የፈተና አፈጻጸሙን ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ፈተናዉን በመውስድ ላይ ያሉ ተማሪዎችንም አበረታተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.