Fana: At a Speed of Life!

አስተዳደሩ ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች በከተማዋ አስተዳደር ስር ባሉ የጤና ተቋማት በሙሉ ነፃ ህክምና እንዲሰጥ መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ 80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ከነፃ ህክምና አገልግሎቱም በተጨማሪ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የጠየቀው መሬት እንዲሰጠው መወሰኑንም ምክትል ከንቲባዋ ማስታወቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

በበአሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ጥረት ባደረገበት ጊዜ ጀግኖች አባቶች እና እናቶች አይበገሬነታቸውን ያስመሰከሩበትን ድል የሚታሰብበት በዓል ነው ብለዋል።

ጣልያን ኢትዮጵያውያንን በዘር፣ በኃይማኖት እና በአካባቢ የመከፋፈል ሴራ ተጠቅሞ ኃይላችንን በማሳነስ ድል ለማድረግ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ጀግኖች አርበኞች የጠላትን ሴራ ቀድመው በመረዳታቸው ውጥኑ ሊከሽፍ እንደቻለ ወይዘሮ አዳነች አስታውሰዋል።

ጀግኖች አርበኞች ባደረጉት ማስተዋል የተመላበት ትግል ትውልዱ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄድባት፣ የሚኮራባት አገር እንዲኖረው አድርገዋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ከጀግኖች አርበኞች መማር ያለባቸው የጠላትን የመከፋፈል ሴራ በማስተዋል እና አንድነትን ማጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።

በስነ-ስርአቱ ላይ ወጣቶች ሽለላና ቀረርቶ ያቀረቡ ሲሆን የማርሽባንድ ትርኢትም ቀርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.