Fana: At a Speed of Life!

3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በጋምቤላ ክልል በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ጋምቤላን እናልብሳት 3ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ “የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “እንደባለፉት ዓመታት ሁሉ ነዋሪዎችን አስተባብረን በመስራት ጋምቤላን ብሎም ሀገሪቱን አረንጓዴ የማድረግ ግባችንን አጠናክረን የምናስቀጥልበት ይሆናል” ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገሮች ጭምር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እቅድ መያዙን አስታውሰው ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀጠናዊ ህብረት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው÷ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሀገር አቀፍ ዕቅድ ውስጥ ለ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኝ መትከያ ቦታ ለክልሉ የተሰጠ ቢሆንም ከዕቅዱ በላይ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የአረንጓዴ ልማት አሻራውን ከግብ ለማድረስ የአመራሩ፣ የባለድርሻ አካላት፣ የባለሙያውና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባ ማመላከታቸውን ከክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ በሀገር አቀፍ ደረጃ 25 ሚሊየን ዜጎችን በማሳተፍ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙ ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.