Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አቤቱታ በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያስገቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አቤቱታ በአንድ አጠቃለውና ፍሬ ነገሮችን እንዲያሟላ አድርገው በሁለት ቀናት ውስጥ ለቦርዱ እንዲያስገቡ አሳሰበ፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት እስካሁን የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራቶችን እያከናወነ ቢሆንም በምርጫው የተወዳደሩ እና በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ፣ በውጤት ቆጠራ እና አገላለጽ ላይ አቤቱታ ያላቸው ፓርቲዎች ያላቸውን አቤቱታ (እስካሁን የቀረበውን ጨምሮ) በአንድ አጠቃልለው እና የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች እንዲያሟላ አድርገው በሁለት ቀናት ውስጥ ለቦርዱ እንዲያስገቡ ያሳሰበ ሲሆን ቅዳሜን እና እሁድንም እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
አቤቱታ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ጉዳዮችም
ድምፅ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ መስፈርት የሚያሟሉ መራጮች እንዳይመርጡ ተከልክለዋል፣ መስፈርት የማያሟሉ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ ብንቃወምም መደበኛ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል ፣ መራጮች አንድን የፖለቲካ ፓርቲ ወይም እጩ እንዲመርጡ ተገድደዋል፣ መራጮች የፈለጉትን ፓርቲ ወይም እጩ እንዳይመርጡ ገደብ እየተጣለባቸው ነው፣ መራጮች በምርጫ አስፈጻሚዎች ጫና እአየተደረገባቸው ነው፣ የምርጫው ሚስጥራዊነት ተጠብቆ ድምፅ የመስጠት ሂደት እየተከናወነ አይደለም፣ ለመራጮች መደለያ እየተሰጠ ነው፤ ምርጫ አስፈፃሚዎች መደለያ እየተቀበሉ ነው፣ የምርጫ ጣቢያው ሕጋዊ ባልሆኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር ወድቋል፣ ታዛቢዎች እና የእጩ ወኪሎች የድምፅ አሰጣጡን ሂደት እንዳይታዘቡ ተከልክለዋል፣ሀሰተኛ የምርጫ ሰነዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፣ የምርጫውን ውጤት የሚጎዳ ሀሰተኛ መረጃ በመሰራጨት ላይ ይገኛል… እና የመሳሰሉት
ከድምፅ ቆጠራና ማዳመር ሂደት ጋር የተያያዘ
በህግ መሰረት ዋጋ አልባ የሆኑ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ወይም የተበላሹ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በመቆጠር ላይ ናቸው ፣ ህጋዊ ድምጽ አላግባብ ዋጋ አልባ እንዲሆን እተደረገ ነው፣የድምጽ መቆጠሩ እና ማዳመሩ ወቅቱን እና ሥርዓቱን ጠብቆ አለመከናወኑ የውጤቱን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፣የድምጽ መስጫ ሳጥን እሽግ ተቀድዷል፣ ተሰብሯል ወይም ብልሽት ደርሶበታል፣ለምርጫ ጣቢያው ከደረሰው የድምጽ መስጫ ወረቀት ብዛት በላይ የሆነ የድምጽ መስጫ ወረቀት ተገኝቷል፣ የድምጽ ቆጠራው እተከናወነ ያለው በሕግ ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ነው፣የድምጽ ቆጠራው በቂ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ብርሃን በሌለበት እንዲከናወን እየተደረገ ነው፤የድምጽ ቆጠራው ሲከናወን ታዛቢዎች፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ወይም የእጩ ወኪሎች እንዳይገኙ ተከልክለዋል ….. እና የመሳሰሉት
ውጤት ይፋ ማድረግን የሚመለከት
የምርጫው ውጤት ለህዝብ እስከአሁን ይፋ አልተደረገም አላግባብ እንዲዘገይ እየተደረገ ነው፣ የምርጫ ጣቢያ ሀላፊው ለግል እጩ ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ ወኪል የውጤት መተማመኛ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ፣የምርጫ ውጤት መግለጫ ቅጾች በአግባቡ እየተሞሉና እየተፈረሙ አይደለም…. እና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ።
2/ የአቤቱታ ይዘት: የድምፅ አሰጣጥ፥ ቆጠራ እና ውጤት አገላለፅን በሚመለከት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚቀርብ አቤቱታ በሶስት ቅጂ ተዘጋጅቶ የሚከተሉትን በማካተት በአቤቱታ አቅራቢው ወይም በወኪሉ ተፈርሞ መቅረብ አለበት፡፡
አቤቱታው የተፃፈበት ቀን ፣ የአቤቱታ አቅራቢው ፓርቲ ሙሉ ስም፣ አድራሻ፣ ሞባይል ቁጥር፣ ኢ-ሜይል፣ ለአቤቱታው መነሻ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ፣ ይህም ምክንያቱን ከመግለፅ በተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ማካተት የሚገባው ሲሆን በተለይ የድምፅ አሰጣጥ፥ ቆጠራ እና ውጤት አገላለፅ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የምርጫ ህጎችን ጥስት የተመለከቱ መሆን ይገባቸዋል በተጨማሪም ጥሰቱ የተፈፀመበትን ቦታ/ ምርጫ ጣቢያ፣ምርጫ ክልል/፤ ቀን እና ሰዓት እና ጥሰቱን የፈፀመውን አካል አካቶ ሊይዝ ይገባል፣ አቤቱታ አቅራቢው እየተጠየቀ ያለውን መፍትሄ በተለይ ማመልከት አለበት ፣የማስረጃ ዝርዝር፣ ይህ ሰነድ ( የጽሁፍ፣ የቪዲዮ፣ የፎቶ) ፣ የሰው ማስረጃዎችን በዝርዝር መያዝ የሚገባው ሲሆን የሚቀርበው የሰው ማስረጃ በሆነ ጊዜ የምስክሮቹን ማንነት እና አድራሻ ዝርዝር አካቶ ሊይዝ ይገባል፥ ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት ጉዳዩ በሌሎች የምርጫ ማስፈፀሚያ አደረጃጀቶች ታይቶ ውሳኔ ተሰጥቶበት ከሆነ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ በሰጡ አካላት የተሰጡ ውሳኔዎች፣ የቀረቡ ማስረጃዎችና የማስረጃ ዝርዝር መግለጫዎች፣ ውሳኔ ካልተሰጠበትም ሁኔታው መጠቀስ ይኖርበታል ተብሏል
ከላይ በተገለፀው መሰረት አቤቱታ ለሚያቀርብ አቤቱታ አቅራቢ በአቤቱታው ቅጂ ላይ ቀንና ሰዓቱ ተመዝግቦ እና ተፈርሞ ማረጋገጫ ይሰጠዋል፡፡
ለአቤቱታው መልስ መስጠት ያለበት ሰው ካለ የዚሁ ሰው ስምና አድራሻ በአቤቱታው ላይ ሊመለከት ይገባል ነው ያለው ቦርዱ።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.