የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ ከዘመቻ ሥራዎች የተሻገረ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ በዘላቂነት ለማስወገድ ከዘመቻ ሥራዎች የተሻገረ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው መጤ የእምቦጭ አረም ለሐይቁ የህልውና አደጋ መኾኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ላለፉት ተከታታይ ዓመታት መንግስት፣ ማኅበራት፣ ግለሰቦች እና የበጎ አድራጎት ተቋማት የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ርብርብ ቢያደርጉም መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣት የሐይቁን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ የመጤ እና ተስፋፊ አረሞች መከላከል ተወካይ ዳይሬክተር መዝገቡ ዳኛው÷ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እምቦጭን በሁለት የተቀናጀ መንገድ ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡
በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች እና 30 ቀበሌዎች የእምቦጭ አረም መከላከል ሥራ ተሰርቷል ያሉት አቶ መዝገቡ÷ ከእነዚህ ውስጥ ለማሽን እንቅስቃሴ የሚመቹት አምስት ቀበሌዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቀሪዎቹ ቀበሌዎች አረሙን በሕዝብ ጉልበት ለማስወገድ ጥረት መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
አረሙ 90 በመቶ ከሐይቁ ላይ መነሳቱን የሚናገሩት ተወካይ ዳይሬክተሩ÷ አበባ እና ፍሬ ሳያፈራ በመታረሙ በሚቀጥለው ዓመት የሚኖረው ስርጭት በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አረሙን ለማስወገድ ከአንድ ሰሞን የዘመቻ ሥራ በመውጣት በየጊዜው ክትትል ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
በያዝነው ዓመት የፌዴራል መንግሥት ተቋማት እና በገንዘብ፣ኢኮኖሚና ትብብር ሚኒስቴር እስከ 70 ሚሊየን ብር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት አቶ መዝገቡ በቀጣይ የተቀናጀ የቴክኒክ እና ሙያ ድጋፍ እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በትብብር አረሙን ከሐይቁ ላይ ለማስወገድ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በምርጫ ሥራዎች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረውን አረም የማጽዳት ሥራ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመርም አቶ መዝገቡ ተናግረዋል፡፡
የእምቦጭ አረምን ከሐይቁ ላይ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከዘመቻ ሥራ የተሻገረ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ መዝገቡ የክልሉ መንግሥት የተሠሩ ሥራዎችን በመከታተል እና አቅጣጫ በመስጠት እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡