Fana: At a Speed of Life!

በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 81 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና በከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሟቾቹ ቁጥር 81 መድረሱ ተገለጸ።

የቻይና ብሄራዊ የጤና ኮሚሽን እንዳስታወቀው በቫይረሱ ከሞቱት በተጨማሪ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 287 ደርሷል።

ከእነዚህ መካከል 461 ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ 5 ሺህ 794 ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀረም አስታውቋል።

ከሰሞኑ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 51ዱ ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ኮሚሽኑ እስከ ትናንት ምሽት ያለውን ሪፖርት ባካተተበት መረጃው ገልጿል።

በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የቻይና መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

ከዚህ ውስጥ የሃገሪቱ የአዲስ ዓመት መለወጫ አከባበርን በሶስት ቀናት እንዲራዘም በትናንትናው እለት ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ቫይረሱ የተቀሰቀሰባት የሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ውሃን እንቅስቃሴ አልባ ስትሆን፥ ሌሎች የቻይና ከተሞችም የጉዞ ክልከላ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኬ ያንግም ቫይረሱ የተቀሰቀሰባትን የሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ውሃንን መጎብኘታቸው ነው የተገለፀው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በቻይና በተቀሰቀሰው ኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ለመወያየት ቤጂንግ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከሶስት ሳምንት በፊት በቻይና ውሃን እንደተከሰተ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ሃገራትም ቫይረሱን ለመከላከል እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል፤ ኢትዮጵያም ኖቭል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምራለች።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.