ሳንባ በሲጋራ ምክንያት ከሚከሰት ጉዳት የማገገም አቅም እንዳለው ተመራማሪዎቹ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳንባ በሲጋራ ምክንያት ከሚከሰት የካንሰር ህመም የማገገም አቅም እንዳለው ተመራማሪዎች ገለጹ።
በለንደን የተደረገው ጥናት ሳንባ በማጨስ ብዛት ከሚከሰት የህዋሳት ጉዳትና ለውጥ የማገገም አቅም እንዳለው አመላክቷል።
ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ለረጅም አመታት ሲጋራ የሚያጨሱ እና ማጨስ ያቆሙ ግለሰቦችን አካተዋል።
በጥናታቸው በሲጋራ ምክንያት ሳንባ ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን ጉዳት በመከታተል ውጤቱን ይፋ አድርገዋል።
በዚህም ሳንባ ረጅም አመት በሲጋራ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት ማገገም ይችላል ብለዋል፤ ይህ የሚሆነው ግን ግለሰቡ/ግለሰቧ ማጨስ ካቆሙ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ማጨስ ያቆሙ ሰዎች ሳንባ፥ ረጅም ጊዜ ሲጋራ በማጨስ ምክንያት በሂደት ከሚከሰት ካንሰር ራሱን የማዳን አቅም አለው።
በጥናቱ በሲጋራ ሳቢያ የተጎዱ የሳንባ ህዋሳት ሰዎቹ ማጨስ ካቆሙ በኋላ ራሳቸውን መተካትናመ ማደስ መቻላቸው ተጠቅሷል።
ማጨስ ካቆሙት ሰዎች የሳንባ ሴሎች ውስጥ 40 በመቶ ያክሉ አጭሰው የማያውቁ ሰዎች ካላቸው የሳንባ ጤንነት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ረጅም አመት አጭሰው ያቋረጡ ሰዎች ከሚያጨሱት አንጻር ጤናማ ሳንባ አላቸው ነው የተባለው።
ተመራማሪዎቹ ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ በሚለው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ያልሰጡ ሲሆን፥ በጉዳዩ ላይ ግን ተጨማሪ ምርምሮች ይደረጋሉ ተብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ