Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የፅዳትና ችግኞችን የመንከባከብ ዘመቻ አከናወኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዳማ ከተማ በስልጠና ላይ የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በከተማዋ የፅዳት እና ችግኞችን የመንከባከብ ዘመቻ አከናወኑ።

ዘመቻው ከስልጠናው በተጓዳኝ በአካባቢው የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና ከተማዋን በማፅዳት ነዋሪውን በአረንጓዴ  ልማት ላይ እንዲሳተፍ ማነቃቃትን ዓላማ የደረገ መሆኑን  የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል።

በክረምት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን ሁኔታ ማየት፣ ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ  የስልጠናው አንዱ አካል መሆኑን የፓርቲው የዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አወሉ አብዲ ተናግረዋል።

አመራሩ ከፖለቲካ ስልጠናው ባለፈ ወደ አካባቢው ሲመለስ ህብረተሰቡ የተከለውን ችግኝ እንዲንከባከብና  የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቋቋም ከወዲሁ መሰረት የሚጥል ተግባር እንዲያከናውኑ በማሰብ ዘመቻው ተካሂዷል ብለዋል።

ወደ ክልላቸውና የአካባቢያቸው ከተሞች ሲመለሱም በዘመቻ መልክ ምን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ማሰብ፣ ማቀድና ለመተግበር መዘጋጀት አስፈላጊ  መሆኑንም ለማስገንዘብ ዘመቻው መከናወኑንም አስረድተዋል።

በአዳማ ከተማና አካባቢዋ ባለፈው የክረምት ወራት ከተተከሉ ችግኞች መካከል 95 በመቶ መፅደቃቸውን  የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ናቸው።

“በከተማዋ ከ12 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ተክለናል” ያሉት ከንቲባው፥ ችግኞቹ እንዳይደርቁ ለከተማዋ ወጣቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ለጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በመስጠትና አጠቃላይ ህብረተሰቡ  እንዲንከባከበው በማድረግ ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ መፅደቁን ተናግረዋል።

ዛሬ የፓርቲው አመራሮች የችግኝ መንከባከብና የፅዳት ዘመቻ ማካሄዳቸው የከተማዋ ህብረተሰብ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራምን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ሞራል የሚፈጥር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በዛሬው የፅዳትና የችግኝ ክብካቤ ዘመቻ ላይ ከ2 ሺህ በላይ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.