በክልሉ ከ361 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ361 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንዲሪስ ገልጸዋል፡፡
የስራ እድል ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል ንግድ፣ አገልግሎት፣ግብርና ፣ማኑፋክቸሪንግ ፣ግንባታ፣የእንስሳት እርባታና ማድለብ፣የመኖ ልማትና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከአንድ ሺህ በላይ የመስሪያና መሸጫ ቦታና የገበያ ሼዶች ለማህበራቱ የተሰጡ ሲሆን÷ ከ40 ሄክታር በላይ ለግብርናና ለተለያየ አገልግሎቶች የሚውል መሬትና የሊዝ ማሽኖችን የክልሉ መንግስት መስጠቱንም አስረድተዋል፡፡
መንግስት በ18 ሺህ 260 ማህበራት ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ወደ 355 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ማቅረብ መቻሉንም አቶ አህመድ አመልክተዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ500 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ቢሆንም÷ የእቅዱን 72 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተናግረዋል።
እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ያልተቻለው የስራ አጥ ወጣቶችን የመለየት፣ የክህሎት ስልጠና መስጠትን ጨምሮ የዝግጅት ምዕራፍ ትልቁን ጊዜ ስለወሰደብን ነው ብለዋል።
ለኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ብድር በወቅቱ ያለመመለስ፣ በስራ ፈላጊው ላይ የሚስተዋለው አመለካከት፣ የስራ አማራጮች ውስንነት በዘርፉ አሁንም የሚታዩ ማነቆዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!