Fana: At a Speed of Life!

ከአልሸባብ ጋር ተቀላቅለው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ እስከ 12 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ተቀላቅለው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ ስምንት ግለሰቦች እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

በሁለት መዝገብ የተከሳሾችን ጉዳይ ተመልክቶና ማስረጃ መርምሮ የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ወንጀል ጅግጅጋ ተዘዋዋሪ ችሎት ነው።

የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች ሀሰን ኢብራሂም (ሀፎ)፣ አማን(ሳለሃዲን) ቃሲም፣ ጂብሪል (ነስረዲን) ራሻ፣ አብዱልሀኪም (ዘይድ) ሁሴን፣ ተማም (ሀምዛ) ሼህ አብዶ፣ አብዲ ጣሂር ኮሌ፣ አደን ሰላድ ካድየ እና መአሊ ድሬ ጉሬ ይባላሉ።

ተከሳሾቹ በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፣ በክልሉ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪዎች ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራ ሲያከናውን እንደነበር ይታወሳል።

በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ተረክቦ በተከሳሾቹ ላይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 2 እና አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በዚህም ባቀረበው ክስ ተከሳሾቹ መቀመጫውን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ያደረገው የአልሸባብ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባል በመሆን ስልጠና በመውሰድ፣ ህዝብን በማሸበር መንግስትን ለማስገደድ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ተቀብለው በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በሶማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ተግባር በመፈጸም እና የሽብር ቡድኑን በመደገፍ እንዲሁም መረጃ በማቀበል ተሳትፎ እንዳላቸው በዝርዝር አስፍሯል።

በጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ በችሎት የክስ ዝርዝሩ በንባብ ተሰምቶ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ክደው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃዎችንና የሰው ምስክሮችን በተለያዩ ቀናቶች በችሎት አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ቢሰጥም ተከሳሾቹ መከላከያ ማስረጃ የለንም በማለት አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብታቸው ታልፎ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየትን እና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየትን በመያዝ በአንደኛ መዝገብ ሀሰን ኢብራሂም (ሀፎ) የተባለ ተከሳሽን በ11 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን÷ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ12 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሁለተኛው መዝገብ ማለትም ለአልሸባብ የሽብር ቡድን መረጃ በማቀበል የሽብር ተግባር ጥፋተኛ የተባሉት አብዲ ኮሌ፣ ጣሂር፣ አደን ሰላድ ካድየ እና ሙአሊ ድሬ ጉሬ የተባሉ ተከሳሾን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ5 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.