Fana: At a Speed of Life!

አቶ ታዬ ደንደአ የፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ የፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍና ጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቧል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው÷ተከሳሹ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስትንና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ድጋፍ የሚገልጹ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ነበር የሚል ነው፡፡

እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽን ኮቭ መሳሪያ ከ2 ክላሽ ካዝና እና ከ60 ጥይት ጋር ይዘው መገኘታቸው ተጠቅሶ ክስ ቀርቦባቸዋል።ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ በአራት ጠበቆቻቸው ተወክለው ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ ተነቦላቸዋል።

ክሱ ከተነበበ በኋላ በጠበቆቻቸው በኩል የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጥያቄ ቀርቧል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄያቸውን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ነጥቦችን ጠቅሶ ተከራክሯል።

ሰበር ሰሚ ችሎት ዋስትናን በልዩ ሁኔታ ሊከለክል የሚችልባቸው ነጥቦች ማለትም በተደራራቢ ክስ መከሰሳቸውን እና የተከሰሱት ድንጋጌ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስጥል ከሆነ ዋስትና ሊያስከለክል ይችላል በማለት ተከራክሯል።

የተከሳሽ ጠበቆችም ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጣቸው ዋስትናን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ድንጋጌዎች ተከሳሹ ላይ በቀረበው ክስ የሚመለከቱ አለመሆናቸው ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ህጻን ልጃቸውን ጥለው የታሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠው የሕጻናት መብት ታሳቢ ተደርጎ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው÷በቁጥጥር ስር ሲውሉ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ገልጸው አቤቱታ በቃል አቅርበዋል።

ምርመራው ታሕሳስ 24 ማለቁንና ዘግይቶ ክስ መቅረቡንም ተቃውመዋል።

ዐቃቤ ሕግ ሌሎች ምርመራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም በአያያዝ ላይ ያቀረቡትን የመብት ጥያቄ በሚመለከት በጽሑፍ በዝርዝር ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል።

ዋስትናውን በሚመለከት መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.