Fana: At a Speed of Life!

ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የሶስቱ ሃገራት ብሄራዊ ገለልተኛ የተመራማሪዎች ቡድን ባዘጋጀው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄድ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኦታዋ የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ጥምረት በካናዳ በጋራ ባዘጋጁት የዌቢናር ስብሰባ ላይ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ችግር ለመቅረፍና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የውሃ ሀብቷን መጠቀም ግዴታዋ በመሆኑ፥ ይኸው ተግባር የታችኞቹን የተፋሰስ ሃገራት በማይጎዳ መልኩ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ ድርሻ ያላት እንደመሆኗ መጠን የህዳሴ የግድብ ግንባታን በዚሁ አግባብ መጀመሯን አስታውሰዋል፡፡

ከግድቡ ጋር ተያይዞ በግብጽና በሱዳን በኩል የሚነሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ በፈረንጆቹ 2015 በሶስቱ ሃገራት መካከል በተፈረመው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፥ መፍትሔ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ተከታታይ ድርድሮች መደረጋቸውን አብራርተዋል።

ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያመጣ የሚታወቅ ቢሆንም በሱዳን እና በግብጽ በኩል ግን ጉዳዩን ዓለም አቀፍ መልክ እንዲይዝ በማድረጋቸው በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን ድርድር እያደናቀፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለቱም ሃገራት የናይል ወንዝ ውሃን በጋራ እና በፍትሃዊነት ከመጠቀም ይልቅ የቅኝ ገዥዎችን ስምምነት ለማጽናት ያላቸው ፍላጎት ለድርድሩ ሂደት ተግዳሮት እንደሆነ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

አሁንም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚደረገወው የሶስትዮሽ ድርድር በውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ አተኩሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.