ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ስኬት አስተዋጽዖ ላደረጉ የምስጋናና እውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት አስፈፃሚዎች ስብሰባ ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት የዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ የምስጋናና የእውቅና መርሐ ግብር አከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ በጉባኤው የተሳተፉ ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እንግዶች የተቀላጠፈና ስኬታማ አቀባበል እንዲሁም አሸኛኘት በማድረግ ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ቀርቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ይህንን ታሪካዊ ሀላፊነትና ክብር በሚመጥን አኳኋን በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
የዝግጅቱ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው በጉባኤው የተሳተፉ ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እንግዶች የተቀላጠፈና ስኬታማ አቀባበልና አሸኛኘተና የተሟላ አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ይህንን ስኬት ላስመዘገቡ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ውብና ማራኪ እንዲሁም ከትራፊክ መጨናነቅ ነፃ እንድትሆን በማድረግ አስተዋፆ ላደረጉ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን በመዲናዋ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት እንዲጎበኙና እንግዶች በጎ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።
በመደበኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከ60 በላይ ተቋማት አስተዋፆ እንዳደረጉ ተመላክቷል።
በታሪኩ ወ/ሰንበት