Fana: At a Speed of Life!

ህዝባችን የጀግንነታችን ምንጭ ነው – ጄኔራል ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ህዝባችን የጀግንነታችን ምንጭ ነው” ሲሉ በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ጄኔራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ።
”ከህዝባችን ጋር ሆነን ‘አዲስ አበባ እገባለሁ’ ብሎ ሲፎክር የነበረውን አሸባሪ ቡድን በወረረው መሬት እንዲቀበር አድርገናል” ሲሉም ገልጸዋል።
ጄኔራል ባጫ ይህን ያሉት የዳያስፖራ አባላት ለተሰዉ እና ለቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ልጆች ትምህርት ቤት ለማስገንባት እንቅስቃሴ በጀመሩበት የውይይት መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ ጄኔራል ባጫ እንዲሁም የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባልና የብሄራዊ ጀግኖች እና ህጻናት አምባ ማህበር የቦርድ አባል ብርጋዴር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፣ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር አዳሙ አንለይ እና የዳያስፖራ አባላት ተገኝተዋል።
ጄኔራል ባጫ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት በጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲና በኢኮኖሚ ትግል ጭምር የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው የከፈቱት እንደዚህ አይነት ጦርነትበታሪኳ ገጥሟት አያውቅም ያሉት ጄኔራሉ፤ ይህን ለመመከት በውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን “ኢትዮጵያ አትበተንም” በማለት በጋራ ቆመው ድል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ህዝቡ በሰው ሀይል፣ በገንዘብ እና በስንቅ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ‘አዲስ አበባ እገባለሁ’ ብሎ ሲፎክር የነበረውን አሸባሪ ቡድን በወረረው መሬት እንዲቀበር ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ዳያስፖራው በዲፕሎማሲና በኢኮኖሚ ግንባር እየተዋጋ አኩሪ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሀገር ጠባቂ በመሆኑ ይህንን ሰራዊት መደገፍ አስፈላጊና ተገቢ ነው ብለዋል።
በተለይ ለተሰዉና ለቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ልጆች ትምህርት ቤት አቋቁሞ መደገፍ አስፈላጊና ተገቢ በመሆኑ ስራውን ቶሎ መጀመር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ በበኩላቸው “ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ከቆምን የውጭ ጠላቶችም ሆነ የሚጋለቡት ፈረሶች አይደፍሩንም” ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላትንም በአንድነት ቆሞ መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው የመጣነው ብሔራዊ ግዴታችንን ለመወጣት በመሆኑ በሚያስፈልገው ሁሉ የበኩላችንን ለማድረግ ቁርጠኞች ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.