Fana: At a Speed of Life!

ለሀገራዊው ምርጫ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ስርጭት መቆጣጠር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) መጭው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ስርጭት መቆጣጠር እንደሚገባ የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማዕከል (ካርድ) አሳሰበ።

በሀገሪቱ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ስርጭት ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስታውቋል።

መንግስት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በማስፈን፣ የተቋማቱን ተዓማኒነት በማሳደግ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤ የሚጨምሩ ስራዎችን በማከናወን የሚመለከታቸው አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ባደረገው የማህበራዊ ትስስር ገጾች ቅኝት፥ በኢትዮጵያ የተደራጁ የመረጃ ማዛባት ስራዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመላክቷል።

ይህ ሁኔታም ሀገራዊ ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት ሊጨምር እንደሚችልም ነው የመብቶች ዴሞክራሲና ብልጽግና ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ ብርሃኔ የተናገሩት።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዜጎች በቂ እና ትክክለኛ መረጃ ኖሯቸው የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፥ ይሁን እንጅ መሰል የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች የዜጎችን በቂ መረጃ የማግኘት መብት ሊያሰተጓጉሉ ይችላሉም ነው ያለው።

ስለሆነም በምርጫ ወቅት መሰል ችግሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ከወዲሁ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይገባዋል ብሏል።

በተጨማሪም ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብም ጥሪ አቅርቧል።

በአፈወርቅ አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.