Fana: At a Speed of Life!

ለተፈናቃዮች ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ በጣሊያንና ግሪክ ከሚገኙ ዳያስፖራዎች ጋር ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለተፈናቃዮች ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ በጣሊያንና ግሪክ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
 
በውይይቱ በጣሊያን እና ግሪክ የሚገኙ ዳያስፖራዎች፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
 
ውይይቱ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች እና በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ አስተባብሮ በሚላክበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
በጣሊያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ ÷ አሸባሪው ህወሓት በአገራችን አንድነት ላይ የደቀነውን አገርን የማፍረስ እኩይ ተግባር እና እየደረሰ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለመመከት ዳያስፖራው እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
 
ጥምር ጦሩ በአሸባሪው ህወሓት ላይ በወሰደው እርምጃ እየተገኘ ያለውን ድል በተመለከተም አምባሳደር ደሚቱ ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
 
በውይይቱ ላይ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ስለ ገንዘብ አሰባሰብ እና መላኪያ መንገዶች ገለጻ አድርገዋል፡፡
 
የቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ሃላፊዎች ስለ አይዞን ኢትዮጵያ መተግበሪያ አጠቃቀም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ የመተግበሪያው አጠቃቀም ተግባራዊ ሙከራ ተደርጎበታል።
 
አምባሳደር ደሚቱ በሮም፣ በግሪክ፣ በፓርማ፣ በቶሪኖ እና በባሪ እየተካሄደ ያለው የገቢ ማሰባሰብ በሌሎች አካባቢዎች እና ከተሞች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
 
የገንዘብ አላላኩን በተመለከተም የአይዞን መተግበሪያን በመጠቀም በቀጥታ ድጋፉን በማዋጣት፣ በየአካባቢው የተሰባሰቡ የድጋፍ ገንዘቦችን በኤምባሲው በኩል ለሚመለከተው አካል ማድረስ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
 
በተጨማሪም በየአካባቢው አንድ ፕሮጀክት (ትምህርት ቤት፣ ቤትና ጤና ተቋማት መልሶ መገንባት) አዋጥተን እንገነባለን ለሚሉ ፕሮጀክቱን በጋራ መምረጥ እና ማስረከብ እንደሚቻል እና አፈፃፀሙ ላይ ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል።
 
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በበኩላቸው፥ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የበኩላቸውን በመወጣት አገራችውንና ወገናቸውን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.