Fana: At a Speed of Life!

ለክልሉ ህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ለክልሉ ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ የምርጫ ጊዜ አንደኛ የስራ ዘመን መስራች ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቋል።

በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት 27 ዓመታት የህወሓት የሽብር ቡድን በዘረጋው የሞግዚት አስተዳደር ህዝቡ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ይልቁንም የሽብር ቡድኑ በነበረው የብሔርና የጎሳ ፖለቲካዊ መዋቅር የክልሉ አመራር ከልማት ይልቅ በጎሰኝነት፣ ጠባብነት፣ ብልሹ አሰራሮች ተንሰራፍተው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ምክንያት የክልሉ እድገትና ልማት ወደ ኋላ ተጓትቶ ህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት።

ባለፉት ዓመታት የታዩት ችግሮች በማስወገድ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠው በማንም ሳይሆን በክልሉ በሚገኙ አመራሮች መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከአዲሱ አመራር የላቀ ቁርጠኝነት ይጠበቃል ብለዋል።

በተለይም የክልሉን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በማንምና በምንም የማይቀለበሰውን የውጥና የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀዋል።

የዘንድሮው አዲስ የመንግስት ምስረታ ልዩ የሚያደርገው የውስጥና የውጪ ጠላቶች በግልጽ ሀገር ለማፍረስ በፈጠሩት ጫና ሳይደናቀፍ በስኬት መካሄዱ ነው ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው÷ ህዝቡ የሰጠውን ኃለፊነትና አደራ በመጠበቅ አዲሱ አመራር ያለውን እውቀትና ልምድ በመጠቀም በታማኝነት ልናገለግለው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

መስራች ጉባኤው በነበረው የግማሽ ቀን ቆይታው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና አፈ-ጉባኤዎችን ጨምሮ ክልሉን በቀጣይ አምስት ዓመት የሚመሩ የስራ ኃላፊዎችን ሹመት አጽድቋል።

በዚህም የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታን ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ ደግሞ ወይዘሮ ትሁት ሐዋሪያትን ሹመት ተሰጥቷል።

እንዲሁም የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ኡሞደ ኡጁሉንና የምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተንኳይ ጆክን የሾመ ሲሆን÷ 21 የካቢኔ አባላትን ሹመት ምክር ቤቱ አጽድቋል።

በተጨማሪም የክልሉን ዋናና ምክትል ኦዲተር፣የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሹመትም መስራች ጉባኤው በማጽደቅ መረሃ ግብሩን ማጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.