Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷መንግስት በመላ ሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የኢመደበኛ ታጣቂዎችንና በሽብር ቡድንነት የተፈረጁ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ይህ የመንግስትና የመላው ጸጥታ ሃይላችን የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን ማዞሩን ነው የገለጸው፡፡

የሽብር ቡድኑ በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች የሰነዘራቸው የሽብር ጥቃቶች በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት ሲከሽፍ በበቀል የሽብር ተግባሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃንን ህይወት በግፍ ቀጥፏል፣ ንብረትንም አውድሟል ብሏል መግለጫው።

ይህ ቡድን በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የሚያሳይ በመሆኑ የጥፋት ሃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልዕኮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሽብር ጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳትም የተሰማውን ልባዊ ሃዘን ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.