በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ76 ሺህ በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፋት 9 ወራት በፍትሐብሔር እና በወንጀል ከቀረቡ 87 ሺህ 600 በላይ መዝገቦች ውስጥ 76 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት ውሳኔ ማግኘታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንዱዓለም አምባዬ አዲስ መዝገቦችን የማስከፈት፣ ቀድሞ የነበሩትን መዝገቦች በአግባቡ የማስተዳደርና እልባት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ከክልሉ ምሥረታ ጀምሮ በዋናው ማዕከል በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ላይ ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ በተዘዋዋሪ ችሎት መስጫ ማዕከላት መዝገብ ከመክፈት እስከ ውሳኔ ዳኝነት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወደፊት ባህላዊ የህግ ፍርድ ቤቶች እንደሚቋቋሙ አመልክተዋል።
ዳኞች ሥራቸውን በነፃነትና ገለልተኝነት እንዲሠሩ የሚያስችሉ አሠራሮች እየተዘረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለመሥራት በእቅድ እየተሠራ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ፍትህ ለሁሉም የሚለውን በተግባር ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች የክልሉ ነዋሪዎች የፍትህ ደላሎችን በማጋለጥ ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ አንዱዓለም አምባዬ አሳስበዋል።
በኢብራሂም ባዲ