Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን አፀደቀ።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባውም የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በስራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ የቆየ በመሆኑ እና የማምረቻ ወጪን መሰረት አድርጎ የሚሰላ በመሆኑ ግልፅነት የሚጎድለው መሆኑን አንስቷል።

ይህን ለማስቀረትም አዲሱ አዋጅ በመሸጫ ዋጋ ላይ እንዲሰላ በማድረግ ለከፋይ እና አስከፋዩ ግልፅነት የሚፈጥር መሆኑን አመላክቷል።

በተጨማሪም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት
ከፍተኛ በመሆኑ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይም ቋሚ ኮሚቴው፥ ከ1 ሺህ 300 ሲሲ ያልበለጠ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ተሽካረካሪዎች እና ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ አዲስ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ፣ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የቀረቡ፣ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ በከፊል ተበትነው የገቡ እና አዲስ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የቀረቡ ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ እንደተደረገበት አንስቷል።

በተጨማሪም ከ1 ዓመት እስከ ከ2 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ80 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲሁም፥ ከ2 ዓመት እስከ ከ4 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ130 በመቶ ወደ 105 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ከ4 እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ230 በመቶ ወደ 205 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉ ተጠቅሷል።

ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ430 በመቶ ወደ 405 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉም ነው የተነሳው።

ይህ ማሻሻያ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

በሲጋራ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በፓኬት በዋጋው 30 በመቶ እንዲሁም በፍሬ 5 ብር የነበረው በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያው ተጨምሮ 8 ብር እንዲሆን መደረጉንም ነው የገለጸው።

በረቂቅ አዋጁ የታሸገ ውሃ ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከ15 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ እንዲጣል በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ ቀርቦ የነበረው የ5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲወጣ መደረጉም ነው የተገለፀው።

በተጨማሪም አዋጁ በማሻሻያው ከፀናበት እለት በፊት የባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው እና አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት እለት አንስቶ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር በሚገቡ እቃዎች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣለው እና የሚሰበሰበው፥ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 በተሻሻለው ድንጋጌዎች መሰረት ይሆናል ተብሏል።

ይህም በአዲሱ ማስተናገድ በታክስ አስተዳደር ስርዓት ላይ ችግር ስለሚያስቀምጥ ገደብ መቀመጡ ተመላክቷል።

ከቅጣት ጋር ተያይዞ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ዝቅተኛውን የቅጣት ገደብ የማያስቀምጥ በመሆኑ አንቀጹ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት የእስር ቅጣት እና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣል በሚል ማሻሻያ እንደተደረገበትም ተገልጿል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁን በ4 ተቃውሞ፣ በ7 ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ የማድረግ የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ልዝርዝር ምርመራ ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ መርቶታል።

በሙለታ መንገሻ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.