Fana: At a Speed of Life!

ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና ይሰራል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ከወንዶች ጋር የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

በሚሊኒየም አዳራሽ ከተማ አቀፍ የሴቶች መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሴቶች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ከወንዶች የሚስተካከሉበትን መንገድ ለመፍጠር ብልጽግና ፓርቲ ይሰራል ብለዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን እንዲሆን የሴቶች እና እናቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች እና እናቶች ስለ ሰላምና አንድነት ማስተማር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከትችት ወጥተው ባላቸው ጊዜ የተለያዩ ማህበራዊ ተሳትፎዎችን በማድረግ ከወዲሁ መስራትን ሊለማመዱት ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የልማት እንቅስቃሴ በሌሎች ከተሞች ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

በንግግራቸው ብልጽግና ፓርቲ የተመሰረተው ከአንድነት ወደ መለያየት መፈጠሩን ተከትሎ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ልማቱ ድህነትን ማጥፋት አለመቻሉም ብልጽግናን መፍጠሩንም ገልጸዋል።

“በህብር ወደ ብልጽግና “በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መድረክ የፌደራልና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስትና የድርጅት ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋ ሴቶች ተሳትፈዋል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.