Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ስራቸውን በአግባቡ ባላከናወኑ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አቶ ሽመልስ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ስራቸውን በአግባቡ ባላከናውኑ የስራ ተቋራጮች እና አማካሪዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልፀዋል።

የ2012 በጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩም የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በዘርፉ ከተሰማሩ የስራ ተቋራጮች እና የግንባታ ፕሮጀክት ካላቸው ሴክተሮች ጋር የፕሮጀክቶችን የስራ አፈፃፀም ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች እና በክልሉ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰማሩ የስራ የቋራጮች እና አማካሪዎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ በክልሉ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ረገድ ችግሮች የነበሩ መሆኑን አንስተው በ2012 በጀት ዓመት ግን የመጨረስ ዘመን በሚል ክልሉ ለዘርፉ በሰጠዉ ከፍተኛ ትኩረትና በተደረገዉ የተቀናጀ ክትትል ከ4 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው ገልፀዋል።

የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በቅድሚያ የፕሮጀክቶችን መጓተት በመቅረፍ በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ማጠናቀቅ ተገቢ መሆኑንም ገልፀዋል።

ፕሮክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ በማያጠናቅቁ የስራ ተቋራጮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የገለፁት አቶ ሽመልስ እስካሁን በ180 የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

እነዚህ የስራ ተቋራጮች በእጃቸው ላይ ያለውን ፕሮጀክቶች እስኪያጠናቅቁ ድረስም ምንም አይነት ጨረታ ላይ መሳተፍ እንደማይችሉም ነው የተነገረው።

በዛሬው እለት 37 በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቶችን ያጠናቀቁ የስራ ተቋራጮች መበረታታቸውን በማንሳት ይህም ይቀጥላል ብለዋል።

በየደረጃው ያሉ የመንግስት መዋቅሮችም በአስፈፃሚነታቸው ላይ ጠንክረው መስራታቸው ለፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ወሳኝነት አንዳለውም ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር መሳይ ዳንኤል በበኩላቸው፥ በ2012 ዓ.ም በዘርፉ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማስተካከል በ2013 ዓ.ም በከፍተኛ ተነሳሽነት ሁሉንም መዋቅሮች በማሳተፍ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቶች መጓተት የህብረሰቡ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ይህንን ለማስተካከልም ከተለመደው አሰራር በተለየ መልኩ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.