Fana: At a Speed of Life!

ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎችን ለአንድነትና ለአገራዊ ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያዊያን ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎችን ለአንድነትና ለአገራዊ ብልፅግና ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ የሕዝብና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች፣ የፌዴሬሽንና የክልል ምክር ቤቶች የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የቀደምት ኢትዮጵያዊያንን ጥበብና የስልጣኔ አሻራ መገንዘብ ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ አገራቸውን ወደ ስልጣኔ ማማ ለማድረስ በአንድነት ታሪክ ሲሰሩ እንደነበረ አመላካች መሆኑንም ገልፀዋል።

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘመነኛ አሰራሮች ባልተስፋፉበት መታነፃቸው ቀደምት አባቶች ለአገራቸው የነበራቸውን ፅናትና ፈተናዎችንም መሻገር እንደሚቻል ትልቅ ምልክት ጥለው ያለፉበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን አሁንም ታሪክ፣ እምነት፣ ባሕልና ወጋቸውን በመጠበቅ አገር ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

አገሪቷ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም ለምጣኔ ሃብት እድገትና አንድነትን ለማጠናከር ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን አውስተዋል።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ አንስተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅርሱን ለመንከባከብና ለማሳደግ ዝግጁ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የወጡ መመሪያዎችን በመተግበር ለምጣኔ ሃብት ያለውን አስተዋጽኦ መጨመር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ በበኩላቸው÷ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያ በርግጥም የስልጣኔ ማማ ላይ እንደነበረች የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ምሑራን ሕዝቦችን በሚያስተሳስሩና አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ታሪካዊ ሃብቶች ላይ በማተኮር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል።

“ቀደምት ኢትዮጵያዊያን ያወረሱንን መልካም ስራዎች እንደ ስንቅ ይዘን ለቀጣይ አገራዊ ግንባታና ብልፅግና ልንጠቀምባቸው ይገባል” ብለዋል።

ከቀደሙ መልካም ታሪኮች በመማር ለቀጣይ የምጣኔ ሃብት እድገት፣ ለሠላም፣ ለአንድነትና ለማኅበራዊ ትስስር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አንዱ የሌላውን ባሕል፣ ታሪክ፣ ወግና ቅርስ ማወቅ፤ መከባበርና መቻቻል አገራዊ አንድነት ለማጠናከርና ለብሔረ መንግስት ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

አዋቂዎችና ጥበበኞች የኖሩባትን አገር ወደነበረችበት ከፍታ ለመመለስ በኅብረትና በቁጭት በመነሳት ዘመናትን የምትሻገር አገር እንገንባ ያሉት ደግሞ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ናቸው።

አባቶቻችን ከሺህ ዓመታት በፊት ያወረሱንን ታሪክ በመጠቀም ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ልዩነትን በማጥበብ ለልጅ ልጆቻችን ታሪክ የምንሰራ እንሁን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.