Fana: At a Speed of Life!

በመተማ ከተማ 150 ሺህ ዶላር ወደ ሱዳን ሊያሸሽ የሞከረ ግለሰብ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር 150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማ አስተዳደተሩ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማንደፍሮ አንለይ እንደተናገሩት ሕገወጥ ዶላሩ የተያዘው ትናንት ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ከመተማ ዮሐንስ ወደ ሱዳን ሊሻገር ሲል በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኬላ በተደረገ ፍተሻ ነው።
በፀጥታ መዋቅሩ ክትትል የተያዘው ተጠርጣሪ ግለሰብ ላይ በመተማ ዮሐንስ ፖሊስ ጣቢያ አስፈላጊው የሕግ ማጣራት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብር ኖቶችን መቀየር ተከትሎ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ሊደረግ የሚችልን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ከሌላው ጊዜ የተለየ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
በቀጣይም ማንኛውም ኅብረተሰብ ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ጥቆማ በመስጠት ሀገር የማዳን ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወደ ሱዳን በሕገወጥ መንገድ የተለያዩ ሸቀጦችና እንስሳት እንዲሁም የግብርና ምርቶች እንዳይሄዱም በኬላዎች የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.