Fana: At a Speed of Life!

በሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የሚቀርቡ ሀሰተኛ ውንጀላዎች የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት ያለሙ ናቸው – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የሚቀርቡ ሀሰተኛ ውንጀላዎች የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት ያለሙ መሆናቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ድጋፉ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ እስካሁን ከ2 ሚሊዮን ለሚልቁት ድጋፍ ሲቀርብ ቀሪዎቹምን ለመድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መንግስት ችግሮችን በመለየት በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፉን ለማድረስ እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በቀጥታ ከመንግስት ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን በአጋር አካላት ደግሞ ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

በዚህም 494 ሺህ ያህል ኩንታል የምግብ እህል፣ የማብሰያ ቁሳቁስ፣ አልሚ ምግቦችና መድኃኒቶች መቅረባቸውን አቶ ደበበ ተናግረዋል።

መንግስት ለትግራይ ክልል እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክቶ በተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኀንና የሰብዓዊ ድርጅቶች እየቀረበ ያለው መረጃ እውነታውን የሳተ መሆኑን የገለጹት አቶ ደበበ፤ በድጋፍ አሰጣጡ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚፈቱበት መዋቅር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

መንግስት በተለይም በመቀሌ ከተማ ካለው የመጠባበቂያ እህል ክምችት በመጠቀም በክልሉ 92 የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ማቋቋሙንና በአሁን ወቅት 82ቱ ጣቢያዎች ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ መሆኑን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከመቀሌ የመጠባበቂያ ምግብ ማከማቻ ጣቢያ ውጪ ወሮታ እና ኮምቦልቻ ከሚገኙ ጣቢያዎችም ሰብዓዊ ድጋፉ እየቀረበ መሆኑን አቶ ደበበ አመልክተዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.