Fana: At a Speed of Life!

በባህርዳር እና አካባቢዋ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ በሚጠናቀቅበት ጉዳይ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በባህርዳር ከተማ እና በዙሪያ ወረዳዎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ በሚጠናቀቅባቸው ጉዳዩች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

በባህርዳር ከተማና በዙሪያ ወረዳ ዘጠኝ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን÷ በጋራ ምክር ቤታቸው በተለያዩ ጉዳዮች ሲመክሩ ቆይተዋል።

በዛሬው ዕለትም አምስት የፓለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት በቅድመ ምርጫ እና በድምፅ መስጫው ቀን ከዚያም በድህረ ምርጫ ሂደት ዙሪያ በጋራ በባህርዳር ከተማ መክረዋል።

የፓርቲ ተወካዮች ከውይይት በኃላ በጋራ ስምምነት በደረሰባቸው አጀንዳዎች ላይ ተመስርተው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጠዋል።

የባህርዳር ከተማ የብልጽግና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ የኔሰው መኮነን ÷የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ብለዋል።

የመኢአድ ባህርዳር ተወካይ አቶ መላኩ በላይ በበኩላቸው አልፎ አልፎ በቅደመ ምርጫ ሂደት የተስተዋሉ ችግሮች ተስተካክለው ምርጫው ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚሳተፍበት እንዲሆን ፓርቲዎች መስራት አለብን ነው ያሉት።

አብንን ወክለው በባህርዳር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው ÷ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ እንዲካሄድ ማድረግ ከፓርቲዎች እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡

የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምንም ወጣቱ ወደ ሁከት መግባት እንደሌለበትም የጠቆሙት ዶክተር ጫኔ ÷መራጩ ህዝብ የድምፅ መስጫ ካርዱን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢዜማ ባህርዳር ዕጩ ተወዳዳሪ ተወካይ አቶ መንግሥቱ ከፍአለም ፓርቲዎቹ የጋራ መግባባት የደረስንባቸውን ጉዳዩች ተግባራዊ ማድረግ አለብን ነው ያሉት፡፡

በነገው ዕለት ለሚካሄደው ምርጫ የህዝብ ድምፅ ማሸነፍ አለበት ያሉት ደግሞ የአዴሃን ተወካይ አቶ ግርማ ተፈራ ናቸው።

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.