Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ህወሓት ፈርሶ የነበረው የአልውሃ ድልድይ ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ፈርሶ የነበረው የአልውሃ ድልድይ ጥገና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
 
ቡድኑ የደረሰበትን ምት መቋቋም ሲያቅተው እና ሲፈረጥጥ የአልውሃን ድልድይ አፍርሶ መሄዱ ይታወቃል።
 
አካባቢው ከአሸባሪው ቡድን ነጻ መሆኑን ተከትሎ የተጀመረው የአልውሃ ድልድይ የጥገና ስራ በዛሬው ዕለት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
 
የአልውሃ ድልድይ ፕሮጀክት መሃንዲስ ኢንጅነር ዮሐንስ አያሌው በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የድልድዩ የጥገና ስራ በሰባት ቀናት ውስጥ ተጠናቋል።
 
የድልድዩ ግንባታም ሙሉ በሙሉ በብረት የተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ 55 ሜትር ርዝመት እንዳለውም ተናግረዋል።
 
ድልድዩም 60 ቶን ወይም 600 ኩንታል የመሸከም አቅም እንዳለውም ጠቅሰው፤ ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የጥገና ስራው እንዲከናወን መደረጉን አመልክተዋል።
 
የድልድዩ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ የቻለውም የኮምቦልቻ ዲስትሪክት የወልድያ ሴክሽን ሰራተኞች ሌት ተቀን በቁጭት ባከናወኑት ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
ድልድዩ ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ጥራቱን ጠብቆ መጠገኑን ገልጸዋል።
 
የአካባቢው ህብረተሰብና አሽከርካሪዎች በድልድዩ መልሶ መገንባትና ለአገልግሎት መብቃት በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.