Fana: At a Speed of Life!

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከኖርዌይ ጋር በትብብር ለመስራት ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ከኖርዌይ የአየር ንብረት እና አከባቢ ሚኒስቴር ልዑካን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሯ የኖርዌይ የአየር ንብረት እና አከባቢ ሚኒስቴር ልዩ ልዑካኑን የመሩትን ሃንስ ብራትስካርን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸውም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አጠቃላይ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የኖርዌይ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አስመልክቶ ስለሚያዘጋጀው የሁለተኛው ምዕራፍ የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ግብዓት የሚሆን የመንግስትን አቅጣጫን በተመለከተም ውይይት ተደርጓል።

ዶክተር ፍጹም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍም ሆነ በአሕጉር ደረጃ የአረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማትን በግንባር ቀደምነት ስታቀነቅን መቆየቷን አስታውሰው÷በእቅድና ፖሊሲ ደረጃ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት ላይ ኢትዮጵያ አጠናክራ መቀጠሏንም አመላክተዋ፡፡

ይህንን ለመደገፍ የመንግስት አደረጃጀት መሻሻሉን እና ሁሉም ዘርፎች የአየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጉዳይን አካተው እንዲያቅዱና እንዲፈጽሙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ሃንስ ብራትስካር በበኩላቸው÷ የኖርዌይ መንግስት ለኢትዮጰያ ሲያደርግ የቆየውን እገዛ በማንሳት÷ በኢንቨስትመንት እና በአየር ንብረት ዘርፍ ኢትዮጵያ የኖርዌይ መንግስት ከሚሰጠው ድጋፍ በአፍሪካ ውስጥ ትልቋ ተጠቃሚ እንደነበረች አንስተዋል።

መንግስታቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ ኢትዮጵያ በቀጠናው ካላት ከፍተኛ ሚና አንፃር በባዮ ዳይቨርሲቲ፣ በደን ልማት እና በዘላቂ ልማት ዙሪያ በሰፊው ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

የተቋማቱ ተወካዮች የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን የሚመለከቱ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.