Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና በቻድ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያና በቻድ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ገለፁ።

ተቀማጭነታቸውን አልጀርስ ሆኖ ቻድ እና ኒጄር የሚሸፍኑት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር ለቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ፥ የሹመት ደብዳቤያቸውን ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር አሚን በኢትዮጵያ እና ቻድ መካከል መልካም የህዝብ ለህዝብ እና ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት መኖሩን በመግለጽ፥ ይህም በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ስላሉት ሀገር በቀል የኢኮሚያ ማሻሻዎች ለፕሬዚዳንቱ ገለጻ ያደረጉት አምባሳደሩ፥ ተጨባጭ የኢካኖሚ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካካል የተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ በሱዳን የነበረውን የፖለቲካ ሂደት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ስለነበራት ጉልህ ድርሻ፣ በደቡብ ሱዳን የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ጥረት እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ጎረቤት ሃገራትን በማቀራረብ ልዮነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ለፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግስታቸው ድጋፍ እንደማይለያቸው ለአምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኘነትን በመዋጋት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገው እንቅስቃሴ በአፍሪካ አህጉራዊ ሰላም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የጎላ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዲሁም በቀጠናው የሚገኙ ጎረቤት ሃገራትን በማቀራረብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያከናወኗቸው የለውጥ ተግባራትን እንደሚያደንቁ በመግለፅ የኖቤል የሰላም ሸልማቱ እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻድን ከሌላው ዓለም ጋር በበረራ በማገናኘት ረገድ እያደረገ ላለው አስተዋዕጾ ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር አሚን በኢትዮጵያ እና በቻድ መካከል ያለውን መልካም፣ ታሪካዊ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.