Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ 6ኛ ሰው ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ስድስተኛ ሰው መገኘቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ውስጥ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሆስፒታሎች እና ከሆቴሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ መሰረትም መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች የ 59 ዓመት የብሪታኒያ ዜግነት ያላት ዲፕሎማት ከሆቴል በተደረገ ጥቆማ በምትገኝበት እራሷን አግልላ እንድትቆይ መደረጉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዲፕሎማቷ በዛሬው ዕለት በተደረገላት የላቦራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዟ መረጋገጡን ነው ዶክተር ሊያ ያስታወቁት።

ከግለሰቧ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የክትትል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ግለሰቧ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላት መሆኑ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በፍጥነት ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ይህንን አውቆ በሁኔታዎች ሳይደናገጥ በተረጋጋ መንፈስ የበሽታውን ስርጭት በመግታት የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.