Fana: At a Speed of Life!

በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልፈታህ ከኩዌት የጃህራ ግዛት አስተዳዳሪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኩዌት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ ከኩዌት የጃህራ ግዛት አስተዳዳሪ ናስር አል-ሀጅራፍ ጋር በሁለትዮሽ እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተወያዩ።

አምባሳደር አብዱልፈታህ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እና ኩዌት ጠንካራ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት ናቸው።

የጃህራግ ዛት አስተዳዳሪ በግዛቲቱ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለሚያደርጉት ጥበቃ ምስጋና አቅርበው ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

አያይዘውም መንግሥት በትግራይ ክልል ያካሄደው ሕግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ዓላማና አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለአስተዳዳሪው አስረድተዋል ።

አሁን ላይ ዘመቻው መጠናቀቁን በመጥቀስም የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን መጠገንና ወደ ሥራ ማስገባት፣ በዘመቻው ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ፣ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋምና ማጠናከር የመንግሥት ትኩረት ተደርገው እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተቋርጠው የነበሩ እንደ ባንክ፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮም፣ ውሃና መብራት የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንደተጀመሩ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ላይ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ለዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

የጃህራ ግዛት አስተዳዳሪ ናስር አል-ሀጅራፍ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፥ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በማህበራዊ ዘርፎች ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ በሚያበረክቱት በጎ አስተዋጽኦ ደስተኛ መሆናቸውንና ፍላጎትንና አቅርቦትን መሰረት በማድረግ ለቀጣይ በሰው ኃይል ሥምሪት ዘርፍ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት የሃገርን ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑንና የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ ለማስከበር በትግራይ ክልል የወሰደውን እርምጃ እንደሚደግፉም አውስተዋል።

በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በድርድር እንዲፈቱ ምኞታቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.