Fana: At a Speed of Life!

በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሁለት ሚሊየን የካናዳ ዶላር በላይ ግምት ያለው የሕክምና ቁሳቁስ አበረከቱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ማስከበር ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከ2 ሚሊየን በላይ የካናዳ ዶላር ወጪ የሆነበት የሕክምና ቁሳቁስ አበረከቱ።

ድጋፉ መቀመጫውን ካናዳ ባደረገው የኢትዮጵያና የካናዳዊያን ኔትዎርክ አድቮኬሲና ማኅበራዊ ድጋፍ ቡድን አማካኝነት ነው።

የቡድኑ ሊቀመንበር ዶክተር ትሁት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት÷በሕግ ማስከበሩ ወቅት አገራቸውን ለማገዝና ለመደገፍ ከተዘጋጁና ቡድኑን መቀላቀል ከሚሹ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት መካሄዱን አስታውሰዋል።

አባላቱ በቅድሚያ በሕግ ማስከበር ተልዕኮ ላይ የተጎዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ማገዝ እንደሚያስፈልግ ማመናቸውን ገልፀዋል።

በዚሁ መሰረት ለድንገተኛና ለተከታታይ ሕክምና የሚያግዝና ወጪው ከ2 ሚሊየን የካናዳ ዶላር በላይ ያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ሊቀመንበሯ አገር ውስጥ ከገባው በተጨማሪ ገሚሱ ከካናዳ እየተጓጓዘ መሆኑን አክለዋል።

ከድጋፉ ባሻገር ስለ ኢትዮጵያ የሚነገሩ የተዛቡና ሃሰተኛ መረጃዎችን ለማጥራት የሚዲያ ቡድን በማቋቋም እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

“በማኅበራዊ ገጾች ኢትዮጵያን በተመለከተትክክለኛ መረጃዎችን ለካናዳ ፓርላማና ለውጭ ግንኙነት ሚኒስትሮች የማስረዳት ስራም እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በካናዳ የሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት በድምጽ፣ በምስልና በጽሁፍ የማድረስ ስራ እየሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።

የቡድኑ አባልና መስራች አቶ ማርቆስ ዘውዴ በበኩላቸው ቡድኑ አገሪቷን በዘላቂነት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር በመሰረተ ልማቶች ላይ አሻራ ለማኖር ዝግጁነት መኖሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ÷ በቡድኑ የተደረገው ድጋፍ በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ቀናኢነት ያሳያል ብለዋል።

የቡድኑ ድጋፍ ጤና ሚኒስቴር የሚያስፈልገውንና ያጋጠመውን የግብዓት እጥረት በመለየት የተደረገ ነው።

ይህም የዳያስፖራውን ተሳታፊነትና ተነሳሽነት የሚያጠናክር በመሆኑ የኢትዮጵያዊያንን እጅ ለእጅ የመያያዝ ባህልን የሚያጠናክር እንደሆነም አክለዋል።

ሌሎች የዳያስፖራ አባላት መሰል ድጋፎችን በማድረግ አብሮነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያና የካናዳዊያን ኔትዎርክ አድቮኬሲና ማኅበራዊ ድጋፍ ቡድን በመላው ካናዳ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተ ነው።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.