Fana: At a Speed of Life!

በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመር አሳሳቢ ሆኗል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሣ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ 615 ሰዎች በፅኑ ዕሙማን መርጃ ክፍል ውስጥ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የ29 ሰዎች ህይወት በቫይረሱ ምክንያት ማለፉንም አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት እየሠፋ፣ በቫይረሱ የመያዝና የመሞት ምጣኔም ከመቸውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም በሃገሪቱ ካለው የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽን ውስንነት ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በህክምና ተቋማት ውስጥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ለህሙማን በወረፋ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በዋናነት መዘናጋትና ቫይረሱን አቅልሎ ማየት፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የቫይረስ መከላከል ትግበራው መቀዛቀዝ እና ፍጹም መዘናጋት ስለሚስተዋል ወረርሽኙ አሁንም ስጋት ሆኖ ቀጥሏልም ነው ያሉት፡፡

ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሕይወቱን መታደግ አለበት ያሉት ዶክተር ተገኔ፥ አመራሩም ርቀትን በመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም እጅን በመታጠብ በዋናነት ለራሱና ለቤተሰቡ እንዲሁም ለሚያገለግለው ህብረተሰብ አርዓያ ሆኖ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ያለመሠላቸት ለተገልጋዮች አስፈላጊ ግብአቶችን በማቅረብና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሊደግፉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማትም ህዝቡን በማስተማር፣ በማስጠንቀቅ፣ በተለያዩ የቫይረሱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና በማስተማር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.