Fana: At a Speed of Life!

በደንገጎ አካባቢ በ10 ሚሊየን ብር ወጪ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሀረማያ ወረዳ ደንገጎ አካባቢ ለሚካሄድ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት 10 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የደንገጎ ዛፍን መሰረት በማድረግ መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ተሰማ ቶሩ ለኢዜአ እንዳሉት÷ፕሮጀክቱ በዋናነት ደንገጎ አቅራቢያ የሚገኘው የአደሌ ሀይቅን ማዕከል አድርጎ 11 ሺህ ሄክታር ቦታ ይሸፍናል።

በአካባቢው የተጎዳው የተፈጥሮ ሃብት መልሶ እንዲያገግም ድሬዳዋ የሚከሰተውን ጎርፍ ለማስቀረትና  የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ በጀት መድበው ስራው እንዲካሄድ እያደረጉ ያሉት የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እንዲሁም ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እንደሆኑም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ከጀመረ  ሁለት ወራት ቢሆንም ቦታውን የማካለል ስራ ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል።

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ የአካባቢው አየር ንብረት እንዲስተካከልና የአደሌ ሀይቅ የውሃ መጠን እንዲጨምር እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በየጊዜው የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ እንዲቀንስ ከማስቻል ባሻገር አካባቢው መዝናኛነት እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢ ሲተገበርም ደንገጎና አካባቢው ተመራጭ ስፍራ እንዲሆን ለማመቻቸት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈዲላ ዳውድ ÷ፕሮጀክቱ ከ17 ዓመታት በኋላ የተመለሰው የሀረማያ ሀይቅ እንዳይደርቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያደሳ በበኩላቸው÷  በክልሉ በተለይም የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲለሙና በደን የተሸፈኑ ስፍራዎችም ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.