Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ በሰጡት መግለጫ÷ በጋምቤላ ክልል በአሁኑ ጊዜ ወቅቱ በጋ በመሆኑ እና ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያጋራው ድንበር ሰፊና ክፍት ስለሆነ የሙርሌ ታጣቂዎች የመግባትና የመውጣት አዝማሚያ አለ ብለዋል።
የሙርሌ ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት ድንበር አቋርጠው በመግባት በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ በካንካን ቀበሌ በከፈቱት ድንገተኛ ተኩስ የ8 ሰዎች ህይወት ወዲያው ሲያልፍ፥ በሌሎች 5 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ክልሉ በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመጠቀም ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብም የታጣቂ ቡድኑን እንቅስቃሴ ነቅቶ በመጠበቅ ለመንግሥት ተገቢውን ጥቆማ ማድረግ እንደሚኖርበት የጠቆሙት ኮሚሽነሩ÷ በደረሰው ጉዳት ሀዘናቸውን መግለጻቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት፥ በኑዌር ዞን እና አኙዋክ ዞኖች ገብተው በርካታ ሕፃናት አፍነው እንደወሰዱ አስታውሰው÷ በወቅቱ ከ170 በላይ ሰዎች ህይወት መለፉን እና ከ2 ሺህ በላይ ከብቶች መውሰዳቸውንም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባት ታፍነው ከተወሰዱት መካከል ከ100 በላይ ሕፃናት ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሱንም አውስተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.