Fana: At a Speed of Life!

በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ-አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ፡፡
 
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በኢትዮጵያ የተደቀነው አደጋ አፍሪካን የማንበርከክ ዓላማ ጭምር ያነገበ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሙከራ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት መሆኗን የገለጸው ኃይሌ፤ ኢትዮጵያን በማንበርከክ የጥቁር ሕዝቦችን አኩሪ ታሪክ ለመቀማት የተቀናጀ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግሯል።
 
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ክብር ወደ ግንባር መዝመታቸው አገሩን ከሚወድ መሪ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርቧል።
 
መላ አፍሪካዊያን ትግሉ የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል፡፡
 
“ኢትዮጵያን ብለን ተሸንፈን አናውቅም፤ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት” ሲል ነው አትሌት ኃይሌ የተናገረው።
በአንድ ወቅት የጎበኛት የቱሪስት መናኸሪያ የነበረችውን የሶሪያዋ አሌፖ ከተማ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት መቀየሯን ጠቅሷል።
 
“በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ላይ ይህን መፍቀድ የለብንም” ያለው አትሌት ኃይሌ፤ “ከዚህ አንጻር ከደጀንነት ባሻገር በግንባር በመሰለፍ ጭምር አገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ለማገልግል ዝግጁ ነኝ” ብሏል፡፡
 
የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ አድዋ ላይ የሰጡትን ነጻነት አሳልፎ መስጠት እንደሌለበት ገልጾ፤ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ተነስተዋል፤ ማንም ሊያቆማቸው አይችልም ነው ያለው፡፡
 
ይህም ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
 
ኢትዮጵያዊያን በግንባር ከመዝመት ባሻገር በደጀንነትም በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም አትሌት ኃይሌ አስገንዝቧል።
 
በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከዚህ ቀደም ከሚሰሩት በእጥፍ በማከናወን በጦርነቱ የጠፋውን ሃብት መተካት አለባቸው ነው ያለው፡፡
 
“የዕለት ተዕለት ተግባራችን አሸባሪው ህወሓት ያወደመውን ሃብትና ለወደፊት ለመልማት ያለንን ውጥን ታሳቢ ያደረግ መሆን አለበት” ሲል ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.