Fana: At a Speed of Life!

በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በአይከል ከተማ በወቅታዊ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ ተጠልለው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀደመ ቀያቸው እየተመለሱ ነው፡፡

ለወራት ያህል ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው በተለያዩ ማቆያዎች ከነበሩ 11ሺህ 938 ተፈናቃዮች መካከል ከ500 በላይ የሚሆኑትን በዛሬው ዕለት የመመለስ ስራ መጀመሩን የአይከል ከተማ ከንቲባ አቶ እንደሻው ክንዴ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባው ለዘመናት በፍቅርና በአብሮነት የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥፋት ሃይሎች ሴራ እርስ በርስ እንዲጋጩና እንዲጎዳዱ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይም የአካባቢውን ሰላም በመመለስና ማህበረሰቡን በማወያየት ተፈናቃዮችን የመመለሱ ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት።

በአማራና ቅማንት ስም ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚፈልጉትን በጋራ እንታገላቸዋለን ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎችም ወገኖቻቸውን በደስታ የተቀበሏቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የአይከል ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መላኩ አለምአንተ በበኩላቸው÷ የፀጥታ ሃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷል ፤ ወደፊትም ይህንን የፀጥታ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

በቀጣይም ቀሪ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ መኖሪያ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በሙሉጌታ ደሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.