Fana: At a Speed of Life!

በ2013 የኦሮሚያ ክልል ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ዝግጀት ተደርጓል- አቶ አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ ፣ጳጉሜን 3 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2013 አዲስ ዓመት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለመድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።

አቶ አዲሱ አረጋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ ከ100 በላይ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 7 አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በ1ኛ ደረጃ ቤቶችም የአጎራባች ክልሎችን ቋንቋዎች እንደ አንድ የትምህርት አይነት ለማስተማር እንዲሁም የገዳ ስርአትን በትምህርት ስርአቱ ለማካተት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ነው ያሉት።

በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎች በምርጫቸው የውጭ ቋንቋዎችንና ባህሎችን እንዲያጠኑም ይደረጋል ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

በክልሉ የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታዎችንም ማጠናቀቅና ለኮሮና ወረርሽኝ ጥንቃቄ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ይሰራል ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት የነበሩ ችግሮች ለማስወገድና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም ስጋት እንዳይሆን ለማስቻል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የ2013 አዲስ ዓመትም የሰላም፤ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆን አቶ አዲሱ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

በትእግስት ስለሺ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.