Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 24 ሰአታት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 106 ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 24 ሰአታት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 106 ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጠው መግለጫ፥ በህብረተሰቡ ዘንድ ከሚስተዋለው የመዘናጋት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ የጋራ ስራ ይጠይቃል ብሏል።

እስካሁን በሁሉም መግቢያ በሮች 668 ሺህ ሰዎች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተናግረዋል።

በዚህም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት 474 መንገደኞች የሁለት ሳምንት የለይቶ ማቆያ ክትትላቸውን ትናንት መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመመርመር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፥ ሁለት ተጨማሪ የላቦራቶሪ ተቋማት በቅርብ ቀናት ውስጥ የምርመራ ውጤታቸውን ይፋ ያደርጋሉም ብለዋል።

ከአሜሪካ የመጡ የመመርመሪያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያዎች ፈቃድ የተሰጣቸው በመሆኑ ለክልሎች የሚበቃ መመርመሪያ እንዲያመርቱ በማድረግ እየተስተዋለ ያለውን የመመርመሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ ይሰራልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ሰዓት 20 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉም ተብሏል።

ከህክምና መስጫ ግብአቶች ጋር በተያያዘም ከዚህ በፊት ከተሰራጩት የህክምና መስጫ ግብአቶች በተጨማሪ ከ2 ሚሊየን በላይ የፊት ጭምብሎች ለሁሉም ክልሎች የተሰራጩ ሲሆን፥ ለ112 የፌደራል መስሪያ ቤቶችም የፊት ጭምብልና የእጅ ጓንት እየተሰራጨ ይገኛል።

በሶዶ ለማ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.