Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ እራሱን በራሱ እያረመ የሚሄድበትን ጠንካራ አደረጃጀት እንደሚያበጅ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ እራሱን በራሱ እያረመ የሚሄድበት ጠንካራ አደረጃጀት እንደሚያበጅ አስታወቀ።

የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ከለውጡ በፊትና በኋላ ያለውን የስራ እንቅስቃሴና የኮሚሽኑ መዋቅር አደረጃጀት ጥናት ላይ በአዳማ እየመከረ ነው።

ዛሬና ነገ በሚቆየው ስብሰባ ላይ የየክልሉ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አመራሮች የሚሳተፉ ሲሆን፥ በቆይታው የእስካሁኑ እንቅስቃሴ ይገመገማል፣ በየክልሉ ያሉ ጥሩ ተሞክሮዎችም ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል።

የቁጥጥር ኮሚሽኑ ኮምሽነር አቶ አወቀ ኃይለማሪያም በመድረኩ መክፈቻ እንዳሉት፥ ከዚህ በፊት የተከሰተውን የፓርቲ ውስጥ ድክመት ያስከተለውን ውድቀት በመጥቀስ አሁን ከዚህ በፊት በኢህአዴግ ዘመን እንደተለመደው የይስሙላ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን መሆን አይችልም ነው ያሉት።

ጠንካራና ፓርቲው እራሱን በራሱ እያረመ እንዲሄድ ማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲሆንም ይሰራል ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ተልዕኮው ምን መምሰል እንዳለበትና የሚሰሩ ስራዎችም በዚህ መድረክ በግልፅ ይቀመጣሉ ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ካሊደ አልዋን በበኩላቸው ኮሚሽኑ እንደ ፓርቲ እራሳችንን የሚናይበት መስታወታችን ነው በማለት፣ ጠንካራ ሆኖ እንዲደራጅም እንደግፋለን ብለዋል።

በሁለት ቀን ቆይታው ኮሚሽኑን በአዲስ ለማደረጀት ታስቦ የተሰራ የመዋቅር አደረጃጀት ጥናት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። ቀጣይ የስራ አቅጣጫም ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፓርቲው ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.