Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት የሚያደርሰውን ጥቃት ለመሸፈን ጩኸቱን ቀጥሎበታል – ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አሸባሪው ህወሓት የሚያደርሰውን ጥቃት ለመሸፈን ጩኸቱን ቀጥሎበታል – ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ማድረሱን እንደቀጠለ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚንስቴሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም÷ ምንም እንኳን በፈረንጆቹ ሰኔ 28 ቀን 2020 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ለሽብር ቡድኑ እድል ለመስጠት ከአንድ ወገን የሆነ የተኩስ አቁም ቢያውጅም÷ ቡድኑ ግን የተሰጠውን የሠላም አማራጭ ከመጠቀም ይልቅ ባልታጠቁ ሠላማዊ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ቡድኑ ውድቀቱን ለመሸፈን እና ህዝባዊ ለማድረግ የትግራይን ህዝብ “ሊያጠቃው ከመጣው ሀይል ለመታደግ ስል የገባሁበት ጦርነት ነው” እያለ የሀሰት መረጃ ሲያሰራጭ ቆይቷል፡፡
አሁን ላይ አሸባሪው ቡድን በያዛቸው ቀጣናዎች ግድያዎች፣ የንብረት ውድመቶች እና ዝርፊያዎች እጅግ ተስፋፍቷል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ከሰሞኑ እንደ አዲስ መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ የከፈተ ሲሆን÷ በተለይም በሰሜን ወሎ እና በአፋር ጭፍራ ንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡
ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እስከ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ በመተኮስ ከ30 የማያንሱ ንጹሃንን መግደሉንም ያስታወቀው መግለጫው አሸባሪ ቡድኑ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እየተጠቀመ ነውም ብሏል፡፡
የሽብር ቡድኑ የማጥቃት ዘመቻ በዋነኛነት ወታደራዊ ኢላማዎችን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ አዛውንቶችን፣ የጦር ጉዳተኞችን እና ሽማግሌዎችንም ማዕከል ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከያዛቸው አካባቢዎች ሽሽት የተፈናቀሉ እና የሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎችም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን መግለጫው አመላክቷል፡፡
ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ ወረራ እና የሽብር ጥቃት እየፈጸመ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት በማስተዋል በወሰደው የተጠናና የታቀደ ጥቃት በመፍረክረኩ፤ ሽንፈቱን ለማካካስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጎጂ በመምሰል የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረበ ነው ሲል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ከፍተኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደገፍ በሰሜን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ እና መግለጫ ፍጹም የተዛባ ነው፡፡
አሜሪካ እና አጋሮቿ በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ገደብ መጣላቸውና ኢትዮጵያን መንግስት ዕርዳታ ማደናቀፍ ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡
እነዚህ አካላት በትግራይ ክልል የስልክ፣ የባንክ እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን በአስቸኳይ ተጠግነው ስራ እንዲጀምሩ፣ ወደ ትግራይ የትራንስፖርት ኮሪደሮች እና የአየር ትስስሮች ሙሉ በሙሉ እንዲጀመር የኢትዮጵያን መንግስት ጠይቀዋል።
ይህ ስህተት ነው፤ በግጭት ውስጥ ሁሉንም ጥፋቶች በአንድ ወገን ላይ ማድረጉ እና ሌላውን ወገን ከበደል ነጻ ማድረጉ ፣ ማድላት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብሏል በመግለጫው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ እንደገለጸው ፣ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሰብዓዊ አገልግሎት ሊውሉ የሚገባቸውን፣ ለወታደራዊ ዓላማዎች መጠቀሙ ፣ለክልሉ ሊደርስ የሚገባው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲጓተት አድርጓል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በትግራይ ክልል አገልግሎት እንደገና ለማስቀጠል በሠሩ በርካታ ዜጎች ላይ የማያቋርጥ ግድያ ሲፈጽም የነበረውን ወያኔ በቀላሉ ማመን አልነበረባቸውም ብሏል።
እነዚህ ሠራተኞች ለሕይወታቸው ዋስትና ሳይኖራቸው በትግራይ ውስጥ እንዲሠሩ ማስገደድ እና በወያኔ የሚደርስባቸው ጥቃት መቀጠሉ ለኢትዮጵያ መንግሥት ፈታኝ ሆኗል።
ወያኔ በአጎራባች አካባቢዎች ከፍተኛ የማጥቃት ዘመቻ እያደረገ ባለበት ወቅት እና ሕዝቡ ጥቃቱን በሚመክትበት ሁኔታ ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ይላካል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ፥ አሜሪካ እና አጋሯ በሚያለቅሰው ተኩላ ወያኔ እንዳይታለሉ እና በሰሜን ወሎ ፣ በጎንደር ፣ በአማራ ዋግ ህምራ እንዲሁም በአፋር ክልሎች የተፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ስቃይ እንዳያሳንሱ ያሳስባል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ፥ አሜሪካ እና አጋሮቿ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በመውሰድና ለህወሓት በማድላት ለቡድኑ የሚያሳዩትን አይዞህ ባይነት እንዲያቆሙ ይፈልጋል።
በተጨማሪም ከትግራይ ውጪ ባሉ አካባቢዎች በህወሓት የተፈፀሙ ጥቃቶችን እና የህዝቦችን ስቃይ ማቃለል ማቆም አለባቸው።
ወያኔ በወታደራዊ ግንባሮች ላይ ሽንፈት ሲሰማው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር አደርጋለሁ በማለት የሚያውለበልበውን የሽንፈት የሰላም ባንዲራ እንዲያውለበለብ ሊፈቀድለት አይገባም ብሏል በመግለጫው።
መንግስት፥ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ ህዳር 04 ቀን 2020 ጀምሮ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ወጥ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን ያካተተ ብሄራዊ ውይይት ለመፍጠር ቁርጠኛ ሲሆን÷ ለኢትዮጵያ የሰላም ትብብር ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.