Fana: At a Speed of Life!

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በ7 ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ ክስ መሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በ7 ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ ክስ ከፈተ።
 
ክሱ በሁለት የተከፈለ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በአምስት ተከሳሾች ላይ የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት ወንጀል ሲሆን በሁለተኛ ክስ ደግሞ 1ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ወንጀል ክስ ነው የተመሰረተው።
 
ከተከሳሾቹ ውስጥ እስክንደር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም፣ አስካለ ደምሌ እና ጌትነት በቀለ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ማለትም አሸናፊ አወቀ እና ፍታዊ ገብረመድህን ባለመያዛቸው አልቀረቡም።
 
አቃቤ ህግ ክሱን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የህገመንግስትና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው የከፈተው።
 
ተከሳሾቹ በሰኔ 23 እና 24 2012 ዓ.ም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ማደራጀትና ማስተባበር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲከናወንባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው።
 
ችሎቱም ክሱ እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን፥ ተከሳሾቹም ከጠበቃ ጋር ተማክረን እንቅረብ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
 
አምስቱም ተከሳሾች በወንጀሉ ድርጊት ተሳትፎ እንደሌላቸው እና በፖለቲካ የሀሳብ ልዩነት እንደተከሰሱ በመግለፅ ፍርድ ቤቱ ፍትሃዊ ሆኖ እንዲመለከትላቸው ጠይቀዋል።
 
ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከጠበቃ ጋር ተማክረው ክሱን ለማንበብ እና አጠቃላይ ዋስትና ላይም ትእዛዝ ለመስጠት ለፊታችን ሀሙስ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
 
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.