Fana: At a Speed of Life!

አጎዋ ካለው ፋይዳ በላይ ትኩረት ተሰጥቶታል – አቶ ክቡር ገና

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የአፍሪካ ሀገራት ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነፃ ወደ ሀገሯ እንዲያስገቡ የሰጠችው እድል አጎዋ ከሚያሰገኘው ፋይዳ በላይ ትኩረት እንደተሰጠው የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ጸሃፊ እና የኢዜማ አመራር አቶ ክቡር ገና ገለጹ፡፡

አቶ ክቡር ገና በፋና ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ቀርበው ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር በተያዘዘ ቆይታ ባደረጉበት ጊዜ እንደተናገሩት፥ አጎዋ በፈረንጆች 2025 የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት እንጂ ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ፕሮጀክት አይደለም።

በመሆኑም ጉዳቱ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ሌሎች አማራጮች ላይ ማተኮሩ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ስትሸጣቸው ከነበሩ ምርቶች ውስጥ ትልቁ ምርት ቡና ነው ያሉት አቶ ክቡር ገና፥ ይህም መቅረቱ ምንም ችግር አያማጣም፤ ምክንያቱም ቡና በየትኛውም ገበያ ተፈላጊ ነውና ብለዋል፡፡

በተለይ ከአፍሪካ ጋር ያለንን የንግድ ግንኙነት ማጠናከሩ ለቀጣይ የንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ስላለው ግንኙነት ሲያነሱም፥ የትኛውም ሀገራት ግንኙነቱን ለመመስረት የሚንቀሳቀሰው ጥቅሙን በሚያስጠብቅ መልኩ መሆኑን በመጠቆም ÷ እነዚህ ሀገራትም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን አንሰተዋል።

ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ያልተቋረጠበት ምክንያት የሚያስቡት የራስ ጥቅም ስላለ ነው ያሉት አቶ ክቡር ገና፥ ለጋራ ጥቅም ሲባል በኢትዮጵያ በኩልም ያለው የዲፕሎማሲ አያያዝን ማስተካከል ይግባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከባድ ጊዚያት ባሳለፈች ጊዜ ምዕራባዊያን ፊታቸውን አዙረውባት ነበር ያሉት አቶ ክቡር ገና፥ እነዚህን ጊዜያቶች ያለፈችው የሀገር ውስጥ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀም ነበር፤ ዛሬም እሱን መንገድ መከተሉ መልካም ይሆናል ብለዋል አቶ ክቡር ገና።

የአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም የውጭ እርዳታን ሳንጠብቅ በራሳችን አቅም የተበላሸውን ማስተካከል ይገባል ይህንንም ከዚህ በፊት ሀገሪቱ አድርጋዋለች ነው ያሉት፡፡

ለተወሰኑ አመታትም ቢሆን ይህን የመልሶ መገንባት እና ተጎጂዎችን የማቋቋም ስራ ለማከናወን የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች የማድረግ ስራንም ሊጠይቅ እንደሚችል አመልክተዋል።

ሌላው እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታየው ደግሞ የአፍሪካዊያን አብሮ የመስራት ፍላጎት ጥሩ እየሆነ መምጣት ነው ያሉት አቶ ክቡር ገና፥ ፍላጎቱ ስላለ ትኩረት ተሰጠቶ ሊሰራበት ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ገለፀዋል።

የሽብር ቡድኑ ካስከተለው ውድመት ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በኢትዮጵያዊያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ወዳጆች በርካታ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙና ይህንን ድጋፍ በተንጠባጠበ ሁኔታ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ ቢመራ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የመልሶ ግንባታ እና ተጎጂዎችን የማቋቋም ሂደቱም ከቀድሞው አሰራር በተለየ ወቅታዊ ችግሩን በሚፈታ መልኩ በተቋም መመራት አለበት ባይ ናቸው።

በአመለወርቅ ደምሰው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.