Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካውያን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ተጠቂዎች ናቸው – ማኪ ሳል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ተጠቂ መሆናቸውን የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል ገለጹ።

ሊቀ መንበሩ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በወቅቱም በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ንፁሃን አፍሪካውያንን ሰለባ ማድረጉን ያነሱት ሊቀ መንበሩ፥ ሩሲያ ይህንን ችግር ለማቃለል የድርሻዋን እንድተወጣ ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን የእህል ምርትና ማዳበሪያን ወደ ውጭ ለመላክ ቃል እንደገቡላቸውም ሊቀ መንበሩ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

40 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ሃገራት የስንዴ ፍጆታ ከሩሲያ እና ዩክሬን የሚመጣ ሲሆን፥ ጦርነቱ የአፍሪካን የስንዴ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የወጪ ምርቶች መላኪያ የሆነው የጥቁር ባህር ወደብ መዘጋቱ የሚታወስ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ አሚን አዋድ “ወደቦችን አለመክፈት ርሃብ ያስከትላል” ሲሉ የገለጹ ሲሆን ፥ የምግብ እጥረት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዜጎችን ሊጎዳና ብዙ ሰዎችን ለስደት ሊዳርግ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ጦርነቱ ቀድሞውኑ በአፍሪካ ከፀጥታ ችግርና የምርት እጥረት ጋር በተያያዘ የነበረውን የእህል አቅርቦት ችግር ያባበሰው ሲሆን ፥ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ግጭት ውስጥ ከገባች በኋላ በአህጉሪቱ የምግብ ዋጋ መጨመሩም ነው የተመላከተው።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ማይክ ደንፎርድ እንዳሉት ፥ ከ80 ሚሊየን በላይ አፍሪካውያን የምግብ ዋስትና እጦት እንደገጠማቸው አንስተዋል።

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት 50 ሚሊየን ገደማ አፍሪካውያን ለምግብ ዋስትና እጦት መዳረጋቸውን በቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር በውይይታቸው ለአህጉራቸው ብቻ ሳይሆን በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በላቲን አሜሪካ ለሚገኙ ሌሎች ሀገራትም ተማጽኗቸውን ለሩሲያው መሪ አቅርበዋል።

ፑቲን በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ሩሲያ በምትቆጣጠራቸው አዞቭ እና ጥቁር ባህር ወደቦች በኩል የዩክሬን እህል ወደ ውጭ ለመላክ ዋስትና ለመስጠት ዝግጁ ናት።

አክለውም ጥሩ የሚባለው መፍትሄ የሩሲያ የቅርብ አጋር በሆነችው በቤላሩስ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በማንሳት እህሉ በዚህ መንገድ እንዲጓጓዝ ማድረግ ነው ብለዋል።

ፑቲን ከስብሰባው በፊት ህልጊዜም ከአፍሪካ ጎን መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ባለፈው አርብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዓለም አቀፉ የዋጋ ንረት ምዕራባውያን ተጠያቂ ናቸው የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ፥ ለዋጋ ጭማሪው ፑቲንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.