Fana: At a Speed of Life!

ታግታ የተወሰደችው ሕፃን በተደረገ የተቀናጀ ክትትል በሦስት ቀናት ውስጥ ተገኘች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታግታ የተወሰደችውን የ2 ዓመት ከ8 ወር ሕፃን የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ጠንካራ ክትትል በሦስት ቀናት ውስጥ መገኘቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የ2 ዓመት ከ8 ወር ዕድሜ ያላት አቢጊያ ዳንኤል የተባለችው ህፃን የታገተችው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሳርቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስዳ እንደሆነ ተገልጿል።

ቸርነት ጥላሁን የተባለው ተጠርጣሪ ከቤተሰቡ ጋር በነበረው ቅርበት ሕፃን አቢጊያን በተለያዩ ቦታዎች እየወሰደ በማዝናናት እንደ ቤተሰቡ አባል ያጫውታት እንደነበረና ከአምስት ወር በላይ ከቤተሰቡ ጋር በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪነት የነበረው ቅርርብ ወንጀሉን በቀላሉ ለመፈፀም ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለትም ነው ፖሊስ የጠቆመው።

ግለሰቡ ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ/ም ከምሽቱ 12 ስዓት ተኩል ገደማ ወደ ህፃኗ ወላጆች መኖሪያ ቤት በመሄድና “እናቷ አምጣት ብላኛለች “ብሎ ለቤት ሰራተኛዋን ከነገረ በሗላ ሕፃን አቢጊያ ዳንኤልን ወስዶ በማገት ገንዘብ እንዲሰጠው ከወላጆቿ ጋር ሲደራደር መቆየቱን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው 150ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንዲሰጠው በመጠየቅ ገንዘቡን ማግኘት ካልቻለ ሕፃኗን በህይወት እንደማያገኟት ሲዝት እንደነበረ የህፃን አቢጊያ ወላጅ እናት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ማስረዳቷም ነው የተነሳው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ሕፃኗን ለማስመለስና ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ቀንና ሌሊት ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ በተደረገው ክትትልም ዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ/ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ዓለም ሰላም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪው ተከራይቶ በሚኖርበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ለሦስት ቀናት ያህል ታግታ የቆየችው ሕፃን ልትገኝ መቻሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ሕፃናት ልጆች ለእንደዚህ ዓይነት ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆኑ እንዲጠብቋቸው አደራ የተሰጣቸው ግለሰቦችም ሆኑ ሞግዚቶችና ወላጆች ነገሮችን በጥርጣሬ በማጤንና የማረጋገጥ ሃላፊነታቸውን በመወጣት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.