Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ጃፓን የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሀገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚው ዘርፍ የጀመሩትን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያስረዱት፡፡

ጃፓን በተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተፈተነችም ቢሆን ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ስለማድረጓ አመስግነው፤ በቀጣይ ለጃፓን የብርሃን ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ በአፍሪካም ሆነ ከአፍሪካ ውጭ በሰላም ማስከበር ከመሳተፍ በስተቀር የትኛውንም ሀገር ሉአላዊነት እንደማትደፍር ያስረዱት ሰብሳቢው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በህዝብ ግፊት የመጣውን ለውጥ የሚፈታተኑ ዘመቻዎች በሀገር ውስጥና ከውጭ እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ጃፓን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ነባራዊ ሁኔታም ሆነ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ያላትን ግልጽ አቋም ተረድታ ለሌሎች አካላት በማሳወቅ አጋርነቷን እድታሳይ ሲሉም አክለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው ሀገራቸው በተለያዩ ጊዜያት በገጠማት ተፈጥሯዊ አደጋ ከተፈጠረው ውድመት ትምህርት በመውሰድ ጠንክራ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጃፓን ህዝብና መንግስት ጎን ለነበረው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል አማባሳደሯ ሰሞኑን በትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማጣራት ወደ ስፍራው ማምራታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና አለም አቀፍ ለጋሾች የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ እያደረጉ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል፡፡

የጃፓን መንግስት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ምግብና የህክምና አገልግሎትን ጨምሮ ለሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች የሚውል 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉንና በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደሯ ቃል ገብተዋል፡፡

በተመሳሳይ ጃፓን እና ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በማጠንከር፤ የግሉ ዘርፍም ተቀራርቦ እንዲሰራ ማበረታታት የሀገራቸው አቋም ስለመሆኑ አምባሳደሯ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.