Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር ሁለተኛዋን የመሬት ምልክታ ሳተላይት ወደ ህዋ ልታመጥቅ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር ሁለተኛዋን የመሬት ምልክታ ሳተላይት ወደ ህዋ ልታመጥቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን በላይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ሳተላይቷ ታህሳስ 10 ቀን 2013 ከቻይና ሳትላይት ማስወንጨፊያ ማእከል ወደ ህዋ ትመጥቃለች።
ሳተላይቷ የመጀመሪያዋ ሳተላይት በመጠቀችበት ወር ቀን እና ሰአትም ኢቲ ስማርት የሚል ስያሜ የተሰጣት ሁለተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ህዋ ትመጥቃለች ነው የተባለው።
የመሬት ምልከታ ሳተላይቷ የግብርና ስራ ላይ በተለይም ድርቅን ለመተንበይ የሚያግዙ መረጃዎችን የምትልክ ሲሆን የመጀመሪያዋ ሳተላይት የማታዳርሳቸውን ቦታዎች በማዳረስ እና ክፍተቶችን በመሙላት ትልቅ ሚና ትጫወታለች ብለዋል ዶክተር ሰሎሞን።
ከ 3 እስከ 4 አመት ህዋ ላይ እድሜ የሚኖራት ይህቺ ሳተላይት ሪሞት ሴንሲንግ ስትሆን 12 ኪሎ ግራም የምትመዝን እና የመጀመሪያዋ ሳተላይት በተቀመጠችበት ከፍታ ላይ የምታርፍ ይሆናል።
ህዋ ላይ በምትገኘው የመጀመሪያ ሳተላይት ከዚህ ቀደም መረጃን ለማግኘት ይወጣ ከነበረው ወጭ ባሻገር፤ በስፔስ ዘርፍ ላይ ሀገራዊ እና አለማቀፋዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ከአለምአቀፍ ተርታ ለመሰለፍ መብቃት መቻሉን ተናግረዋል።
ከተገኙት በርካታ ጥቅሞች በመነሳት እና የህዋ ቴክኖሎጅ ተጠቃሚነትን ለማስፋት አሁንም የሳተላይት ግንባታ ሂደቱ ቀጥሏል ነው ያሉት።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢቲ አር ኤስ ኤስ 2 በፈረንጆቹ 2022 ለማምጠቅ እየተሰራ ሲሆን ትልቅ ወጭን የሚጠይቀው እና በአለም ከፍተኛ መረጃን በመያዝ የሚታወቀው የኮሙኒኬሽን ሳትላይት ባለቤት ለመሆንም ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
በዚህም ባለሙያዎችን ከማፍራት ጀምሮ በሚቀጥሉት 10 አመታት 7 ሳትላይትችን ወደ ህዋ ለማምጠቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ታህሳስ ወር ላይ ለምትመጥቀው ኢቲ ስማርት ሳትላይትም እስካሁን 2 ሚሊየን ዶላር ወጭ ተደርጎል ሲሉ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አስታውቀዋል።
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.