Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የመላውን ጥቁር ሕዝብ ትግል እያካሄደች ነው

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የመላውን ጥቁር ሕዝብ ትግል እያካሄደች መሆኑን የዚምባብዌው ፓን አፍሪካ አቀንቃኝና የታሪክ ባለሙያ ማፖንጋ ጆሹዓ ገለጹ።
ኢትዮጵያን በዘመናት ታሪኳ በምዕራባውያን ፍላጎትና ጫና ሥር ለማስገባት በርካታ ሴራዎች ቢሸረቡም ሁሉንም ችግሮች ተቋቁማ ማለፍ ችላለች።
በተለይም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1884 የበርሊን ሥምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያን ለማስገበር የመጣው የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ያደረገውን ወረራ ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት ተመው የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ሕልም በአድዋ ተራሮች ላይ አምክነው የአገሪቷን ነጻነት ማስጠበቅ መቻላቸውን አውስተዋል።
ዳግም ለብቀላ የመጣው ፋሺስት ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ውርደትን ተከናንቦ የተመለሰ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን አይበገሬነት፤ አልንበረከክም ባይነት ዳግም አስመስክሯል።
አሁን ደግሞ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የአገሪቷን ሉዓላዊነት እየተጋፉ መሆኑን ምሁራን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳይ በራሷ ውሳኔ እንዳትሰጥ ማዕቀብ ጭምር በመጣል እጅ እየጠመዘዙና የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በምዕራባዊያኑ አገራት የሚዘወሩት ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በትሮይ ፈረስነት የኢትዮጵያን መንግሥት ቅቡልነት ለመሸርሸር በቀዳሚነት መሰለፋቸውንም ጠቁመዋል።
የዚምባብዌው ፓን አፍሪካኒስት አቀንቃኝ ማፖንጋ ጆሹዓ እንደተናገሩት፤ የምዕራባውያኑ ዓለም አሁን ላይ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተዋል ብለዋል።
ጦርነቱን ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከመላው አፍሪካ ጋር መሆኑንም ነው ያነሱት።
በመሆኑም አፍሪካውያን በአንድነት በመቆም በተለይም የአፍሪካ ህብረት በምዕራቡ ዓለም የሚካሄደውን የተቀነባበረ ሴራ መከላከል እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በተለይም አንድ የአፍሪካ አገር መንካት ማለት ሙሉ አፍሪካን መንካት መሆኑን መላው የአህጉሪቱ ሕዝብ ሊያውቀውና ሊገነዘበው እንደሚገባ አንስተዋል።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ የመንግሥት ግልበጣ ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸው፤ ይህ አይነቱ ሴራቸው ነገ ከነገ ወዲያ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ሊቃጣ እንደሚችል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ዴንማርካዊው የፖለቲካ ምሁር ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን በበኩላቸው ምዕራባዊያን በሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን እውነታ በተሳሳተ መልኩ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውንና ከፍተኛ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለውን መንግሥት ለማንኳሰስ የማጠልሸት ሥራ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ነጻ አገር ሆና የቆየች መሆኗን አንስተው በአገሪቷ ያለውን ችግር በሯሷ አቅም መፍታት የምትችለው በመሆኑ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ተናግረዋል።
መላው የጥቁር ሕዝብም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም “ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ” ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪ መላውን የጥቁር ሕዝብ እንደሚያነሳሳና ትግሉ አህጉራዊ ይዘት እንደሚኖረው የተናገሩት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው።
ይህም አፍሪካዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለመከላከል እንደሚያስችላቸው ጠቁመው ይህንን የምዕራቡ ዓለም ጫና ለማቃለል የሚያስችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.